[1] እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያየሁ አይደለሁምን? እናንተስ በጌታችን ሥራዬ አይደላችሁምን?
[2] ለሌሎች ሐዋርያቸው ባልሆንም ለእናንተስ ሐዋርያችሁ እኔ ነኝ፤ በጌታችን የሐዋርያነቴ ማኅተም እናንተ ናችሁና።
[3] ለሚከራከሩኝ መልሴ እንዲህ ነው።
[4] በውኑ ልንበላና ልንጠጣ አይገባንምን?
[5] እንደ ሌሎች ሐዋርያት ሁሉና፥ እንደ ጌታችን ወንድሞች እንደ ኬፋም ከሴቶች እኅታችንን ይዘን ልንዞር አይገባንምን?
[6] ወይስ ሥራን ለመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን?
[7] የሚያገለግልም ምግቡን ያገኝ ዘንድ ነው፤ ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? መንጋውንስ ጠብቆ ወተቱን የማይጠጣ ማን ነው?
[8] በውኑ ለሰው ይምሰል እናገራለሁን? የሙሴ መጽሐፍ ኦሪትስ እንዲህ ብሎ የለምን ፥
[9] “እህልህን በምታበራይበት ጊዜ የበሬውን አፉን አትሰረው።” እንግዲህ ይህን የጻፈ ለእግዚአብሔር በሬ አሳዝኖት ነውን?
[10] ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን? የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ፥ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው በእውነት ስለ እኛ ተጽፎአል።
[11] እኛ መንፈሳዊውን ነገር ከዘራንላችሁ ሥጋዊውን ነገር ብናጭድ ታላቅ ነገር ነውን?
[12] በእኛ ሹመት ሌላ የሚቀድመን ከሆነ የሚሻላችሁን እናንተ ታውቃላችሁ፤ እኔ ይህን አልፈለግሁትም፤ ነገር ግን የክርስቶስን ትምህርት እንዳላሰናክል በሁሉ እታገሣለሁ።
[13] የጣዖታቱ ካህናት የጣዖታቱን መባ እንደሚበሉ አታውቁምን? መሠዊያውን የሚያገለግሉም መሥዋዕቱን እንደሚካፈሉ አታውቁምን? ለቤተ እግዚአብሔር ሹሞች መተዳደሪያቸው የቤተ እግዚአብሔር መባ ነው።
[14] ጌታችንም እንዲሁ ወንጌልን ለሚያስተምሩ ሰዎች ለሕይወታቸው መተዳደሪያ በዚያው ወንጌልን በማስተማር ይሆን ዘንድ አዘዘ።
[15] እኔ ግን ይህንም ቢሆን አልፈቀድሁትም፤ ይህን የጻፍሁም ይህን እንዳገኝ ብዬ አይደለም፤ እኔ ግን ምስጋናዬ ከሚቀርብኝ ሞት ይሻለኛል።
[16] ወንጌልን ባስተምርም መመስገን አይገባኝም፤ ታዝዤ አድርጌዋለሁና፤ ወንጌልን ባላስተምር ደግሞ ወዮልኝ።
[17] ይህንስ በፈቃዴ አድርጌው ብሆን ዋጋዬን ባገኘሁ ነበር፤ በግድ ከሆነ ግን በተሰጠኝ መጋቢነት አገለገልሁ።
[18] እንግዲህ ዋጋዬ ምንድን ነው? ወንጌልን ባስተምርም በሹመቴ የማገኘው ሳይኖር ወንጌልን ያለ ዋጋ እንዳስተምር ባደርግ ነው።
[19] እኔ ከሁሉ ይልቅ ነጻ ስሆን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት እሰበስባቸው ዘንድ እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛሁ።
[20] አይሁድን እጠቅማቸው ዘንድ ለአይሁድ እንደ አይሁዳዊ ሆንሁላቸው፤ ከኦሪት በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ እኔ ራሴ ከኦሪት በታች ሳልሆን ከኦሪት በታች ላሉት ከኦሪት በታች እንዳለ ሰው ሆንሁላቸው።
[21] የእግዚአብሔርን ሕግ የዘነጋሁ ሳልሆን፥ በክርስቶስ ሕግም ሳለሁ ሕግ የሌላቸውን እጠቅማቸው ዘንድ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለው ሆንሁላቸው።
[22] ደካሞችንም እጠቅማቸው ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁላቸው፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶቹን አድን ዘንድ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ።
[23] በወንጌልም ትምህርት አንድነት ይኖረኝ ዘንድ ስለ ወንጌል ትምህርት ሁሉን አደርጋለሁ።
[24] በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሽቀዳደሙ ሁሉ እንደሚፋጠኑ አታውቁምን? ለቀደመው የሚደረግለት ዋጋ አለ፤ እንዲሁ እናንተም እንድታገኙ ፈጽማችሁ ሩጡ።
[25] የሚታገል ሁሉ በሁሉ ነገር ይታገሣል፤ እነርሱስ የሚጠፋውንና የሚያልፈውን የምስጋናቸውን ዋጋ አክሊል ያገኙ ዘንድ ይበረታሉ፤ እኛ ግን የማያልፈውን አክሊል ለማግኘት እንታገሣለን።
[26] እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፤ ነፋስንም እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም።
[27] ነገር ግን ለሌላ ሳስተምር፥ እኔ ለራሴ የተናቅሁ እንዳልሆን ሰውነቴን አስጨንቃታለሁ፥ ሥጋዬንም አስገዛዋለሁ።