Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 8:05

[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ያስተማርኋችሁንና የተቀበላችሁትን ያላችሁበትን፥ በእርሱም የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ።

[2] ያስተማርኋችሁን ታስቡ እንደ ሆነ በቃሌ አስተምሬአችኋለሁ፤ ያለዚያ ግን ማመናችሁ ከንቱ ነው።

[3] እኔ የተማርሁትን አስቀድሜ መጽሐፍ እንደሚል እንዲህ ብዬ አስተማርኋችሁ ፥ “ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ።

[4] ተቀበረ፤ እንደ ተጻፈም በሦስተኛው ቀን ተነሣ።”

[5] ለጴጥሮስ ታየው፤ ከዚህም በኋላ ለዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርቱ ታያቸው።

[6] ከዚህም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታያቸው፤ ከእነርሱ ብዙዎቹ እስከ ዛሬ አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል።

[7] ከዚህም በኋላ ለያዕቆብ ታየው፤ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ፤

[8] ከሁሉም በኋላ ጭንጋፍ ለምመስል ለእኔ ታየኝ።

[9] ከሐዋርያት ሁሉ እኔ አንሣለሁና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስለ አሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፥

[10] ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን እኔ ባለሁበት አለሁ፤ ለእኔም የሰጠኝ ጸጋው ለከንቱ የሆነብኝ አይደለም፤ እኔም ከሁሉ ይልቅ ደከምሁ፤ ነገር ግን በእኔ ላይ ያደረው የእግዚአብሔር ጸጋ አጸናኝ እንጂ እኔ አይደለሁም።

[11] አሁንም እኔም ብሆን፥ እነርሱም ቢሆኑ እንዲህ እናስተምራለን፤ እናንተም እንዲሁ አምናችኋል።

[12] ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶአል ብለን ለሌላው የምናስተምር ከሆነ፥ እንግዲህ ከመካከላችሁ ሙታን አይነሡም የሚሉ እንዴት ይኖራሉ?

[13] ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስም ከሙታን ተለይቶ አልተነሣማ፤

[14] ክርስቶስም ከሙታን ካልተነሣ እንግዲያስ ትምህርታችን ከንቱ ነው፤ የእናንተም እምነታችሁ ከንቱ ነው።

[15] እኛም በእግዚአብሔር ላይ የሐሰት ምስክሮች ሆነናል፤ ክርስቶስን አስነሣው ብለናልና፥ እንግዲያ ሳያስነሣው ነውን?።

[16] ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስም ከሙታን አልተነሣማ።

[17] ክርስቶስም ከሙታን ካልተነሣ ማመናችሁ ከንቱ ነው፤ ገናም በኀጢአታችሁ አላችሁ።

[18] እንግዲያስ በክርስቶስ አምነው የሞቱ ጠፍተዋላ።

[19] በዚህ ዓለም ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ከአደረግነው ከሰው ሁሉ ይልቅ ጉዳተኟች ነን።

[20] አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአል።

[21] በመጀመሪያው ሰው ሞት መጥቶአልና፤ በሁለተኛው ሰው ትንሣኤ ሙታን ሆነ።

[22] ሁሉ በአዳም እንደሚሞት እንዲሁ በክርስቶስ ሁሉ ሕያዋን ይሆናሉ።

[23] ነገር ግን ሰው ሁሉ በየሥርዐቱ ይነሣል፤ በመጀመሪያ ከሙታን የተነሣ ክርስቶስ ነው፤ ከዚያ በኋላ በክርስቶስ ያመኑ እርሱ በሚመጣበት ጊዜ ይነሣሉ።

[24] እግዚአብሔር አብ መንግሥቱን እጅ ባደረገ ጊዜ፥ ገዥም ሁሉ፥ ንጉሥም ሁሉ፥ ኀይልም ሁሉ በተሻረ ጊዜ፥ ያንጊዜ ፍጻሜ ይሆናል።

[25] ጠላቶቹ ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪወድቁ ድረስ ይነግሥ ዘንድ አለውና።

[26] ከዚያ በኋላ የመጨረሻው ጠላት ይሻራል፤ ይኸውም ሞት ነው።

[27] ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶለታልና፥ “ሁሉ ይገዛለት ” ባለ ጊዜ ግን ሁሉን ከሚያስገዛለት በቀር እንደ ሆነ የታወቀ ነው።

[28] ሁሉም በተገዛለት ጊዜ ግን እግዚአብሔር በሁሉ ቦታ በሁሉ ይሆን ዘንድ፥ ያን ዕለት ወልድም ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።

[29] ያለዚያማ ለምን ያጠምቃሉ? ሙታን እንዲነሡ አይደለምን? ሙታን የማይነሡ ከሆነስ ለምን ያጠምቃሉ?

[30] እንግዲህ እኛስ ሁልጊዜ መከራን ስለምን እንቀበላለን?

[31] ወንድሞቻችን ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነውና በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክህት ሁልጊዜ እገደላለሁ።

[32] በውኑ በኤፌሶን ከአውሬ ጋር የታገልሁ ለሰው ብዬ ነውን? ምንስ ይጠቅመኛል? ሙታን የማይነሡ ከሆነ እንግዲህ እንብላ እንጠጣ፥ ነገም እንሞታለን።

[33] ወንድሞቻችን አያስቱአችሁ፤ ክፉ ነገር መልካም ጠባይን ያበላሻልና።

[34] ለጽድቅ ትጉ፤ አትሳቱ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁት ሰዎች አሉና፤ ነገር ግን እንድታፍሩ ይህን እላችኋለሁ፤

[35] ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚነሡስ በምን አካላቸው ነው? የሚል አለ።

[36] አንተ ሰነፍ! አንተ የምትዘራው እንኳን ካልፈረሰ አይበቅልም።

[37] የምትዘራውም የስንዴ ቢሆን፥ የሌላም ቢሆን የምትዘራት ቅንጣት ብቻ ናት እንጂ ይህ ኋላ የሚገኘው አገዳው አይደለም።

[38] እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አገዳን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱ ዘርም አገዳው እየራሱ ነው።

[39] የፍጥረቱ ሁሉ አካል አንድ አይደለምና፤ የሰው አካል ሌላ ነው፤ የእንስሳም አካል ሌላ ነው፤ የወፍ አካልም ሌላ ነው፤ የዓሣ አካልም ሌላ ነው።

[40] ሰማያዊ አካል አለ፤ ምድራዊ አካልም አለ፤ ነገር ግን በሰማይ ያለው አካል ክብሩ ልዩ ነው፤ በምድርም ያለው አካል ክብሩ ልዩ ነው።

[41] የፀሐይ ክብሩ ሌላ ነው፤ የጨረቃም ክብሩ ሌላ ነው፤ የከዋክብትም ክብራቸው ሌላ ነው፤ ኮከብ ከኮከብ በክብር ይበልጣልና።

[42] የሙታን ትንሣኤያቸው እንዲሁ ነው፥ በሚፈርስ አካል ይዘራል፤ በማይፈርስ አካል ይነሣል።

[43] በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፤ በኀይል ይነሣል።

[44] ሥጋዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል፤ ሥጋዊ አካል አለና መንፈሳዊ አካልም ደግሞ አለ።

[45] መጽሐፍ እንዲሁ ብሎአልና የመጀመሪያው ሰው አዳም በነፍስ ሕያው ሆኖ ተፈጠረ፤ ሁለተኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው።

[46] ነገር ግን አስቀድሞ ሥጋዊው፥ ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ፥ መንፈሳዊው መጀመሪያው አይደለም።

[47] መጀመሪያው ሰው ከመሬት የተገኘ መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ ነው።

[48] መሬታውያኑ እንደዚያ እንደ መሬታዊው ናቸው፤ ሰማያውያኑም እንደዚያ እንደ ሰማያዊው ናቸው።

[49] የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን እንዲሁ የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን።

[50] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ይህን እንነግራችኋለን ፥ ሥጋዊና ደማዊ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፥ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን አይወርስም።

[51] እነሆ፥ አንድ ምሥጢርን እነግራችኋለሁ፥ ሁላችን የምንሞት አይደለም።

[52] ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን እንደ ዐይን ጥቅሻ በአንድ ጊዜ እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋል፤ ሙታንም የማይፈርሱ ሁነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን።

[53] ይህ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን፥ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ይለብስ ዘንድ አለውና።

[54] ይህ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን በለበሰ ጊዜ፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በለበሰ ጊዜ፤ “ሞት በመሸነፍ ተዋጠ ” ተብሎ የተጻፈው ያንጊዜ ይፈጸማል።

[55] “ሞት ሆይ፥ እንግዲህ መውጊያህ ወዴት አለ? መቃብር ሆይ፥ አሸናፊነትህ ወዴት አለ?”

[56] የሞት መውጊያ ኀጢአት ናት፥ የኀጢአትም ኀይልዋ ኦሪት ናት።

[57] በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ድል መንሣትን ለሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።

[58] አሁንም የተወደዳችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ የጸናችሁና የማትናወጡ ሁኑ፤ ዘወትር በጎ ምግባርን አብዝታችሁ ለእግዚአብሔር አበርክቱ፤ ስለ ጌታችን መድከማችሁ ለከንቱ እንዳይደለ ታውቃላችሁና።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 — Chapters