Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:51

[1] ስለ ጻፋችሁልኝስ ለሰው ወደ ሴት አለመቅረብ ይሻለዋል።

[2] ነገር ግን እንዳትሴስኑ ሰው ሁሉ በሚስቱ ይወሰን፤ ሴትም ሁላ በባልዋ ትወሰን።

[3] ለሚስትም ባልዋ የሚገባትን ያድርግላት፤ እንዲሁ ሚስትም ለባልዋ የሚገባውን ታድርግለት።

[4] ሚስት በራስዋ አካል ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ባል በራሱ አካል ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ።

[5] ለጸሎት እንድትተጉ ከምትስማሙበት ጊዜ ብቻ በቀር፥ ባልና ሚስት አትለያዩ፤ ዳግመኛ ሰይጣን ድል እንዳያደርጋችሁ በአንድነት ኑሩ፤ ሰውነታችሁ ደካማ ነውና ።

[6] ይህንም የምላችሁ እንደ ፈቃድ ነው እንጂ፥ ላዝዛችሁ አይደለም።

[7] ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ እግዚአብሔር እንደ አደለው ጸጋ ይኑር፤ ግብሩ እንዲህ የሆነ አለና፤ ግብሩ ሌላ የሆነም አለና።

[8] ነገር ግን ያላገቡትንና አግብተው የፈቱትን እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ ይሻላቸዋል እላለሁ።

[9] መታገሥ ባይችሉ ግን ያግቡ፤ በፍትወት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና።

[10] ያገቡትንም በእግዚአብሔር ትእዛዝ አዝዛቸዋለሁ፤ በራሴ ትእዛዝም አይደለም፤ ሚስትም ከባልዋ አትፋታ።

[11] ከተፋታችም ብቻዋን ትኑር፤ ያለዚያ ከባልዋ ጋር ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን አይፍታ።

[12] ሌላውን ግን ከራሴ እናገራለሁ፤ ከጌታችንም አይደለም፤ ከወንድሞቻችን መካከል የማታምን፥ ባልዋንም የምታፈቅር ከእርሱም ጋር ለመኖር የምትወድ ሚስት ያለችው ሰው ቢኖር ሚስቱን አይፍታ።

[13] ሴቲቱም የማያምንና ሚስቱንም የሚያፈቅር ከእርስዋም ጋር ሊኖር የሚወድ ባል ቢኖራት ባልዋን አትፍታ።

[14] የማያምን ባል በሚስቱ ይቀደሳልና፤ የማታምን ሚስትም በባልዋ ትቀደሳለችና፤ ያለዚያማ ልጆቻቸው ርኩሳን ይሆናሉ፤ አሁን ግን ቅዱሳን ናቸው።

[15] የማያምን ግን ቢፈታ ይፍታ፤ ወንድምና እኅት እግዚአብሔር ለሰላም ስለ ጠራቸው እንደዚህ ላለ ግብር አይገዙምና።

[16] ሚስትም ባልዋን ታድነው እንደ ሆነ አታውቅምና፤ ባልም ሚስቱን ያድናት እንደ ሆነ አያውቅምና።

[17] ነገር ግን ሁሉ እግዚአብሔር እንደ አደለው፥ ሁሉም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይኑር፤ ለአብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ እንዲህ ሥርዐት እንሠራለን።

[18] ተገዝሮ ሳለ የተጠራ ቢኖር አለመገዘርን አይመኝ፤ ያልተገዘረም ቢጠራ ከዚያ ወዲያ አይገዘር።

[19] የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ መገዘርም አይጠቅምም፤ አለመገዘርም አይጎዳም።

[20] ሁሉ እንደ ተጠራ እንዲሁ ይኑር።

[21] አንተ ባርያ ሳለህ ብታምን አያሳዝንህ፤ የሚቻልህ ከሆነ ግን ነጻነትህን አግኝ።

[22] የተጠራ ባሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነጻነት ያለው ነውና፤ እንዲሁ ነጻነት ያለውም ከተጠራ የክርስቶስ ባርያ ነው።

[23] በዋጋ ገዝቶአችኋልና የሰው ተገዦች አትሁኑ።

[24] ወንድሞቻችን ሁላችሁም በተጠራችሁበት እንዲሁ በእግዚአብሔር ኑሩ።

[25] ስለ ደናግልም የምነግራችሁ የእግዚአብሔር ትእዛዝ አይደለም፤ ታማኝ እንድሆን እግዚአብሔር ይቅር ያለኝ እንደ መሆኔ ምክሬን እነግራችኋለሁ እንጂ።

[26] ነገር ግን እንዲህ ይመስለኛል፤ በግድ ይህ ሊመረጥ ይሻላልና እንዲህ ሆኖ ቢኖር ለሰው ይሻለዋል።

[27] ከሚስትህ ጋር ሳለህ ከእርስዋ መፋታትን አትሻ፤ ሚስት ከሌለህ ግን ሚስትን አትሻ።

[28] ብታገባም ኀጢአት አይሆንብህም፤ ድንግሊቱም ባል ብታገባ ኀጢአት አይሆንባትም፤ ያገቡ ግን ለራሳቸው ድካምን ይሻሉ፤ እኔም ይህን የምላችሁ ስለማዝንላችሁ ነው።

[29] ነገር ግን ወንድሞቻችን እንዲህ ይቀናል፤ የዚህ ዓለም ኑሮ ሁሉ ሊያልፍ ቀርቦአልና፤ አሁንም ያገቡ እንዳላገቡ ይሆናሉ።

[30] ያለቀሱ እንዳላለቀሱ ይሆናሉ፤ ደስ ያላቸውም ደስ እንዳላላቸው ይሆናሉ፤ የሸጡም እንዳልሸጡ ይሆናሉ፤ የገዙም እንዳልገዙ ይሆናሉ።

[31] የበሉ እንዳልበሉ ይሆናሉ፤ የጠጡም እንዳልጠጡ ይሆናሉ፤ የዚህ ዓለም ተድላ ሁሉ ያልፋልና።

[32] እኔስ ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ፤ ያላገባ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኘው የእግዚአብሔርን ነገር ያስባልና።

[33] ያገባ ግን ሚስቱን ደስ ሊያሰኝ የዚህን ዓለም ኑሮ ያስባል።

[34] እንዲህ ከሆነ ግን ተለያየ፤ አግብታ የፈታች ሴትም ያላገባች ድንግልም ብትሆን ነፍስዋም ሥጋዋም ይቀደስ ዘንድ እግዚአብሔርን ታስበዋለች፤ ያገባች ግን ባልዋን ደስ ልታሰኝ የዚህን ዓለም ኑሮ ታስባለች።

[35] ይህንም የምላችሁ እንዲጠቅማችሁ ነው፤ ላጠምዳችሁ ግን አይደለም፤ ኑሮአችሁ አንድ ወገን እንዲሆንና እግዚአብሔርን ያለመጠራጠር እንድታገለግሉት ነው እንጂ።

[36] በሸመገለ ጊዜ ስለ ድንግልናው እንደሚያፍር የሚያስብ ሰው ቢኖር እንዲህ ሊሆን ይገባል፤ የወደደውን ያድርግ፤ ቢያገባም ኀጢአት የለበትም።

[37] በልቡ የቈረጠና ያላወላወለ ግን የወደደውን ሊያደርግ ይችላል፤ ግድም አይበሉት፤ ድንግልናውንም ይጠብቅ ዘንድ በልቡ ቢጸና መልካም አደረገ።

[38] ድንግሊቱን ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባ ግን የምትሻለውን አደረገ።

[39] ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሠረች ናት፤ ባልዋ የሞተ እንደ ሆነ ግን ነጻ ናት፤ የወደደችውን ታግባ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ይሁን።

[40] በምክሬ ጸንታ እንዲሁ ብትኖር ግን ብፅዕት ናት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 — Chapters