[1] እንግዲህ በሚነቅፉ ሰዎች ዘንድ ልትከራከሩ አትድፈሩ፤ ከጓደኛው ጋር በዐመፀኟች ዘንድ ሊከራከር የሚችል አለን? በደጋጎች ዘንድ አይደለምን? ከባልንጀራው ጋር ክርክር ያለው ቢኖርም በቅዱሳን ዘንድ ይከራከር፤ በሚነቅፉና በዐመፀኟች ዘንድ ግን አይደለም።
[2] ቅዱሳን ሰውን ሁሉ እንደሚዳኙ አታውቁምን? እናንተ ሰውን ሁሉ የምትዳኙ ከሆናችሁ ይህን ትንሹን ነገር ልትዳኙ አይገባችሁምን?
[3] የዚህንስ ዓለም ዳኝነት ተዉትና በመላእክት ስንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን?
[4] ነገር ግን የዚህ ዓለም ክርክር ያላቸው ሰዎች ቢኖሩ በቤተ ክርስቲያን የተሾሙ የበታች ወንድሞች ይስሙአቸው።
[5] ይህንም የምላችሁ ስዘልፋችሁ ነው፤ እንግዲህ ከመካከላቸሁ ወንድማማቾችን ከወንድሞቻቸው ጋር ማስታረቅ የሚችል ሽማግሌ የለምን?
[6] ነገር ግን ወንድም ከወንድሙ ጋር ይካሰሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋል።
[7] እንግዲህ ፀብና ክርክር ካላችሁ፥ ከመጀመሪያው ጀምሮ ውርደት እንደሚሆንባችሁ ዕወቁ፤ እንግዲያማ እንዴት አትነጠቁም? እንዴትስ አትገፉም?
[8] አሁንም ቢሆን፥ እናንተ ዐመፀኟችና ቀማኟች ናችሁ፤ እንደዚህም ወንድሞቻችሁን ትበድላላችሁ።
[9] ዐመፀኟች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? አያስቱአችሁ፤ ሴሰኟች፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ፥ ወይም አመንዝራዎች፥ ወይም ቀላጮች፥ ወይም በወንድ ላይ ዝሙትን የሚሠሩ፥ የሚሠሩባቸውም ቢሆኑ፤
[10] ሌቦች፥ ወይም ቀማኟች፥ ወይም ሰካሮች፥ ወይም ተሳዳቢዎች፥ ወይም ነጣቂዎች፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱአትም።
[11] እንግዲህ እናንተ እንዲህ ስትሆኑ እነማን ናችሁ? ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋልም።
[12] በሆነው ሁሉ ላይ ሥልጣን አለኝ፤ ግን ሁሉ የሚጠቅመኝ አይደለም፤ ሁሉም ይቻለኛል፤ ነገር ግን በእኔ ላይ እንዲሠለጥን የማደርገው ምንም የለም።
[13] መብል ለሆድ ነው ፤ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ይሽራቸዋል፤ ሥጋችሁም ለእግዚአብሔር ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ እግዚአብሔርም ለሥጋችሁ ነው።
[14] ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው እግዚአብሔር እኛንም በከሃሊነቱ ያስነሣናል።
[15] ሥጋችሁ የክርስቶስ አካል እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን አካል ወስዳችሁ የአመንዝራ አካል ታደርጉታላችሁን? አይገባም።
[16] ከአመንዝራ ጋር የተገናኘ ከእርስዋ ጋር አንድ አካል እንዲሆን አታውቁምን? መጽሐፍ ፥ “ሁለቱ አንድ አካል ይሆናሉ ” ብሎአልና።
[17] ከእግዚአብሔር ጋር የተዋሐደ ግን ከእርሱ ጋር አንድ መንፈስ ይሆናል።
[18] ከዝሙት ራቁ፤ ኀጢአት የሚሠራ ሰው ሁሉ ከሥጋው ውጭ ይሠራልና፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን ራሱ በሥጋው ላይ ኀጢአትን ይሠራል።
[19] ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር ለተቀበላችሁት በእናንተ አድሮ ላለ ለመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ለራሳችሁም አይደላችሁም።
[20] በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን በሥጋችሁ አክብሩት።