Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:00

[1] የሰውን ሁሉ ቌንቌ ባውቅ፥ የመላእክትንም ሁሉ ቌንቌ ባውቅ፥ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ እንደሚጮህ ነሐስ፥ ወይም እንደሚመታ ከበሮ መሆኔ ነው።

[2] ትንቢት ብናገር፥ የተሰውረውን ሁሉ፥ ጥበብንም ሁሉ ባውቅ፥ ተራራ እስከ ማፍለስ የሚያደርስ ፍጹም እምነትም ቢኖረኝ ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።

[3] ገንዘቤን ሁሉ ለምጿት ብሰጥ፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል ብሰጥ፥ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።

[4] ፍቅር ያስታግሣል፤ ፍቅር ያስተዛዝናል፤ ፍቅር አያቀናናም፤ ፍቅር አያስመካም፤ ፍቅር ልቡናን አያስታብይም።

[5] ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፤ አያበሳጭም፤ ክፉ ነገርንም አያሳስብም።

[6] ጽድቅን በመሥራት ደስ ያሰኛል እንጂ፥ ግፍን በመሥራት ደስ አያሰኝም።

[7] በሁሉ ያቻችላል፤ በሁሉም ያስተማምናል፤ በሁሉም ተስፋ ያስደርጋል፥ በሁሉም ያስታግሣል።

[8] ፍቅር ለዘወትር አይጥልም፤ ትንቢት የሚናገርም ያልፋል፤ ይሻራልም፤ በልዩ ልዩ ቌንቌ የሚናገርም ያልፋል፤ ይቀራል፤ የሚራቀቅም ያልፋል፤ ይጠፋል።

[9] በየገጹ ጥቂት ጥቂት እናውቃለንና፤ ጥቂት ጥቂት ትንቢትም እንናገራለንና።

[10] ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ያ ተከፍሎ የነበረው ይሻራል።

[11] እኔ ልጅ በነበርሁ ጊዜ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅም አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም እመክር ነበር፤ በአደግሁ ጊዜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሁሉ ሻርሁ።

[12] አሁን ግን ታወቀኝ፤ በግልጥም ተረዳኝ፤ በመስታወትም እንደሚያይ ሰው ዛሬ በድንግዝግዝታ እናያለን፤ ያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ አሁን በከፊል፥ ኋላ ግን እንደ ተገለጠልኝ መጠን ሁሉን አውቃለሁ።

[13] አሁንም እነዚህ ሦስቱ እምነት፥ ተስፋና ፍቅር ጸንተው ይኖራሉ፤ ከሁሉ ግን ፍቅር ይበልጣል።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 — Chapters