Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:06

[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታም ታውቁ ዘንድ እንጂ አላዋቆች ልትሆኑ አንወድድም።

[2] ቀድሞም እናንተ አሕዛብ በነበራችሁ ጊዜ ዲዳዎች ጣዖታትን ታመልኩ እንደ ነበር፥ ጣዖትም በማምለክ ረክሳችሁ እንደ ነበር፥ ወደ ወሰዱአችሁም ትሄዱ እንደ ነበር ታውቃላችሁ።

[3] ስለዚህም ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር ፥ “ኢየሱስ ውጉዝ ነው ” የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር “ኢየሱስ ጌታ ነው ” ሊል አንድስ እንኳን እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ።

[4] መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው።

[5] ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ።

[6] ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ።

[7] ለሁሉም ጌታ እየረዳ በየዕድሉ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳንዱ በግልጥ ይሰጠዋል፤

[8] በመንፈስ ቅዱስ የጥበብ ቃል የሚሰጠው አለ፤ በመንፈስ ቅዱስም የዕውቀት ቃል የሚሰጠው አለ።

[9] ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥

[10] ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል።

[11] በዚህም ሁሉ ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ይረዳል፤ ለሁሉም እንደ ወደደ ያድላቸዋል።

[12] አካል አንድ እንደ ሆነ ብዙ የአካል ክፍሎችም እንደ አሉበት፥ ነገር ግን የአካል ክፍሎች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤

[13] እኛ ሁላችንም በአንድ መንፈስ አንድ አካል ለመሆን ተጠምቀናል፤ አይሁድ ብንሆን፥ አረማውያንም ብንሆን፥ ባሪያዎችም ብንሆን፥ ነጻዎችም ብንሆን ሁላችን አንድ መንፈስ ጠጥተናልና።

[14] የአካላችንም ክፍሉ ብዙ ነው እንጂ አንድ አይደለም።

[15] እግርም ፥ “እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ” ብትል ይህን በማለቷ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን?

[16] ጆሮም ፥ “እኔ ዐይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ” ብትል ይህን በማለቷ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን?

[17] አካል ሁሉ ዐይን ቢሆን ኖሮ መስማት ከየት በተገኘ ነበር፤ አካልስ ሁሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮ ማሽተት ከየት በተገኘ ነበር?

[18] አሁን ግን እግዚአብሔር የአካላችንን ክፍል በሰውነታችን ውስጥ እርሱ እንደ ወደደ እየራሱ አከናውኖ መደበው።

[19] የአካል ክፍሉ አንድ ቢሆን ኖሮ አካል የት በተገኘ ነበር?

[20] አሁንም የአካል ክፍሎች ብዙዎች ናቸው ፤ አካሉ ግን አንድ ነው።

[21] ዐይን እጅን ፥ “አልፈልግሽም ” ልትላት አትችልም፤ ራስም ፥ “እግሮችን አልፈልጋችሁም ” ልትላቸው አትችልም።

[22] ደካሞች የሚመስሉህ የአካል ክፍሎች ይልቁን የሚያስፈልጉህ ናቸው።

[23] ከአካልም ክፍሎች የተናቁ ለሚመስሉን ክብርን እንጨምርላቸዋለን፤ ለምናፍርባቸውም የአካል ክፍሎች ክብር ይጨመርላቸዋል።

[24] ለከበረው የአካላችን ክፍል ክብርን አንሻለትም፤ እግዚአብሔር ግን ሰውነታችንን አስማምቶታል፤ ይልቁንም ታናሹን የአካል ክፍል አክብሮታል።

[25] የአካላችን ክፍሎች እርስ በርሳቸው እንዳይለያዩ፥ አካላችን ሳይነጣጠል በክብር እንዲተካከል አስማማው።

[26] አንዱ የአካል ክፍል ቢታመም ከእርሱ ጋር የአካል ክፍሎች ሁሉ ይታመማሉ፤ አንዱ የአካል ክፍል ደስ ቢለውም የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።

[27] እንግዲህ እናንተ የክርስቶስ አካሉ ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ክፍሎች ናችሁ።

[28] እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የሾማቸው አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም መምህራንን፥ ከዚህም በኋላ ተአምራትና ኀይል ማድረግ የተሰጣቸውን፥ ቀጥሎም የመፈወስ ሀብት የተሰጣቸውን፥ የመርዳትም ሀብት የተሰጣቸውን፥ የመምራትና ቌንቌን የመናገር ሀብት የተሰጣቸውን ነው።

[29] በውኑ ሁሉ ሐዋርያትን ይሆናሉን? ሁሉስ ነቢያትን ይሆናሉን? ሁሉስ መምህራንን ይሆናሉን? ለሁሉስ ተአምራትን የማድረግ ኀይል ይሰጣልን?

[30] ለሁሉስ የመፈወስ ሀብት ይሰጣልን? ሁሉስ በቌንቌ ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጕuማሉን?

[31] ነገር ግን ለምትበልጠው ጸጋ ቅኑ፤ ደግሞም የምትሻለውን መንገድ አስተምራችኋለሁ።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 — Chapters