[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔም ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በማባበልና ነገርን በማራቀቅ የእግዚአብሔርን ትምህርት ላስተምራችሁ የመጣሁ አይደለም።
[2] ከተሰቀለው ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር በእናንተ ዘንድ ሌላ ነገር እሰማለሁ ብዬ አልጠረጠርሁም ነበር።
[3] እኔም በድካምና በፍርሀት፥ በብዙ መንቀጥቀጥም መጣሁ።
[4] ቃሌም፥ ትምህርቴም መንፈስንና ኀይልን በመግለጥ ነበር እንጂ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።
[5] ማመናችሁ በእግዚአብሔር ኀይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን።
[6] ለዐዋቆች ጥበብን እንነግራቸዋለን፤ ነገር ግን የዚህን ዓለም ጥበብ ወይም ያልፉ ዘንድ ያላቸውን የዚህን ዓለም ሹሞች ጥበብ አይደለም።
[7] ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔር ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።
[8] የዚህ ዓለም ሹሞችም አላወቁትም፤ ይህንስ ቢያውቁ ኑሮ የክብር ባለቤትን ባልሰቀሉትም ነበር።
[9] ነገር ግን መጽሐፍ ፥ “ዐይን ያላየው፥ ጆሮም ያልሰማው፥ በሰውም ልቡና ያልታሰበ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ነው።” ብሎ የለምን?
[10] ለእኛም እግዚአብሔር በመንፈሱ ገለጠልን፤ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ምሥጢሩን ያውቃልና።
[11] በሰው ልቡና ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? በእርሱ ያለችው ነፍሱ ናት እንጂ፤ እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን አሳብ የሚያውቅ የለም።
[12] እኛ የዚህን ዓለም መንፈስ የተቀበልን አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋ እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሚሆነውን መንፈስ ተቀበልን።
[13] ይህም ትምህርታችን ከሰው የተገኘ ትምህርት አይደለም፤ የአነጋገር ጥበብም አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስ የገለጸው ትምህርት ነው እንጂ፤ መንፈሳዊ ጥበብም ከመንፈስ ቅዱስ የሚሆነውን መርምረው ለሚያውቁ ለመንፈሳውያን ነው።
[14] ለሥጋዊ ሰው ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ይመስለዋልና፥ አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቅ አይችልም።
[15] መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል፤ እርሱን ግን የሚመረምረው የለም።
[16] የእግዚአብሔርን አሳብ ማን ያውቃል? መካሩስ ማን ነው? እኛ ግን ክርስቶስ የሚገልጠው ዕውቀት አለን።