Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:06

[1] እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ።

[2] ወንድሞቼ ሆይ፥ አመሰግናችኋለሁ፤ ዘወትር ታስቡኛላችሁና፤ ያስተማርኋችሁንም ትምህርት ጠብቃችኋልና።

[3] ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራሱ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስዋ ወንድ፤ የክርስቶስም ራሱ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወድዳለሁ።

[4] ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም የሚያስተምር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል።

[5] ራስዋን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም የምታስተምር ሴት ሁላ ራስዋን ታዋርዳለች፤ ራስዋን እንደ ተላጨች መሆንዋ ነውና።

[6] ሴት ካልተከናነበች ትላጭ ወይም ጠጕuርዋን ትቈረጥ፤ ለሴት ጠጕuርዋን መቈረጥ ወይም መላጨት ውርደት ከሆነ ትከናነብ።

[7] ወንድ በሚጸልይበት ጊዜ ሊከናነብ አይገባውም፤ የእግዚአብሔር አርአያውና አምሳሉ ነውና፤ ሴትም ለባልዋ ክብር ናት።

[8] ሴት ከወንድ ተገኝታለችና፤ ወንድ ግን ከሴት የተገኘ አይደለም።

[9] ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረም፤ ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ።

[10] ስለዚህም ሴት ስለ መላእክት፥ ሥልጣን ለራስዋ ሊሆን ይገባል፤

[11] ነገር ግን አሁን ሴት ከባሏ አትለይ፤ ወንድም ከሚስቱ አይለይ፤ ሁላችሁም በጌታችን ኑሩ።

[12] ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች እንዲሁ ወንድ ከሴት ተገኘ፤ ነገር ግን ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው።

[13] እስኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ፤ ሴት ወደ እግዚአብሔር በምትጸልይበት ጊዜ ልትከናነብ አይገባምን?

[14] ተፈጥሮዋስ አያስረዳችሁምን? ወንድ ግን ጠጕuሩን ቢያሳድግ ነውር ነው።

[15] ለሴት ግን ጠጕuርዋን ብታሳድግ ክብርዋ ነው፤ ለሴት ጠጕuርዋ እንደ ቀጸላ ሆኖ ተሰጥቶአታልና።

[16] ነገር ግን የሚጠራጠር ቢኖር እኛ ወይም የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ልማድ የለንም።

[17] ይህንም የነገርኋችሁ ላመሰግናችሁ አይደለም፤ በምትሰበሰቡበት ጊዜ ወደ ዝቅተኛ እንጂ ወደሚሻል ግብር አትሄዱምና።

[18] ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን በምትሰበሰቡ ጊዜ እንደምትጣሉና እንደምትከራከሩ ሰምቻለሁ፤ የማምነውም አለኝ።

[19] ከእናንተ የተመረጡት ወንድሞች ተለይተው እንዲታወቁ ትለያዩ ዘንድ ግድ ነው።

[20] እንግዲህ እናንተም በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉና የምትጠጡ ለጌታችን ቀን እንደሚገባ አይደለም።

[21] ወደ ምግብ ትሽቀዳደማላችሁ፤ የተራቡ በአጠገባችሁ እያሉ እናንተ ትበላላችሁ፤ ትጠግባላችሁ፤ ትሰክራላችሁም።

[22] በውኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ታስነቅፋላችሁን? ነዳያንንስ ታሳፍሩአቸዋላችሁን? ምን እላለሁ? በዚህ አመሰግናችኋለሁን? አላመሰግናችሁም።

[23] ከእግዚአብሔር እንደ ተማርሁ አስተምሬአችኋለሁና፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ራሱን በያዙባት በዚያች ሌሊት ኅብስቱን አነሣ።

[24] አመሰገነ፤ ባረከ፤ ፈተተ፤ እንዲህም አላቸው ፥ “እንኩ ብሉ፤ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ መታሰቢያዬንም እንዲሁ አድርጉ።”

[25] እንዲሁም ኅብስቱን ከተቀበሉ በኋላ ጿውን አንሥቶ ፥ “አዲስ ሥርዐት የሚጸናበት ይህ ጿ ደሜ ነው እንዲህ አድርጉ፤ በምትጠጡበትም ጊዜ አስቡኝ ” አላቸው።

[26] ይህን ኅብስት በምትበሉበት፥ ይህንም ጿ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታችን እስከሚመጣበት ቀን ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።

[27] አሁንም ሳይገባው ይህን ኅብስት የበላ፥ ይህንም ጿ የጠጣ የጌታችን ሥጋውና ደሙ ስለሆነ ዕዳ አለበት።

[28] አሁንም ሰው ራሱን መርምሮና አንጽቶ ከዚህ ኅብስት ይብላ፤ ከዚህም ጿ ይጠጣ።

[29] ሳይገባው፥ የጌታችን ሥጋም እንደ ሆነ ሳያውቅ፥ ሰውነቱንም ሳያነጻ፥ የሚበላና የሚጠጣ ለራሱ ፍርዱንና መቅሠፍቱን ይበላል፤ ይጠጣልም።

[30] ስለዚህ ከመካከላችሁ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች ናቸው፤ ብዙዎችም በድንገት አንቀላፍተዋል።

[31] እኛ በራሳችን ብንፈርድ ኖሮ ባልተፈረደብንም ነበር።

[32] ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኰነን በጌታ እንገሠጻለን።

[33] አሁንም ወንሞቻችን ሆይ፥ ለምሳ በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ፤

[34] መሰብሰባችሁ ለፍዳ እንዳይሆን፥ የተራበ ቢኖር በቤቱ ይብላ፤ አትነቃቀፉም፤ ሌላውን ሥርዐት ግን መጥቼ እሠራላችኋለሁ።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 — Chapters