Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:49

[1] እኛ የክርስቶስ አገልጋዮችና የእግዚአብሔር የምሥጢሩ መጋቢዎች እንደ ሆን ሰው ስለ እኛ እንዲህ ያስብ።

[2] እንግዲህ በዚህ ከመጋቢዎች እያንዳንዱ ቸርና ታማኝ ሆኖ እንዲገኝ ይፈለጋል።

[3] ለእኔስ በእናንተ ዘንድ መመስገን ውርደት ነው፤ ጻድቅ ብትሉኝ፥ በመዋቲ ሰው ዘንድም ቸር ብላችሁ ብታከብሩኝ እኔ ለራሴ አልፈርድም።

[4] የሚያጠራጥረኝና ትዝ የሚለኝ ነገር የለም፤ በዚህም ራሴን አላመጻድቅም፤ እግዚአብሔር ይመረምረኛልና።

[5] ጊዜው ሳይደርስ ዛሬ ለምን ትመረምራላቸሁ? በጨለማ ውስጥ የተሰወረውንም የሚያበራ፥ የልብን አሳብም የሚገልጥ ጌታችን ይመጣል፤ ያንጊዜ ሁሉም ዋጋውን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል።

[6] ወንድሞቻችን ሆይ! እኔም፥ አጵሎስም ብንሆን መከራ የተቀበልነው ስለ እናንተ ነው፤ እናንተ እንድትማሩ፥ ከመጻሕፍት ቃልም ወጥታችሁ በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳትታበዩ ነው።

[7] ማን ይመረምርሃል? የምትታበይስ በምንድን ነው? ከሌላ ያላገኘኸው አለህን? ያለህንም ከሌላ ካገኘህ እንዳላገኘ ለምን ትኮራለህ?

[8] እናንተ አሁን ጠግባችኋል፤ በልጽጋችኋልም፤ ያለእኛም ፈጽማችሁ ነግሣችኋል፤ እኛም ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ አግባብ በሆነ ነበር።

[9] እኔስ ለሞት ዝግጁዎች እንደ መሆናችን እኛን ሐዋርያቱን እግዚአብሔር የኋለኟች ያደረገን ይመስለኛል፤ እኛ ለሰዎችም፥ ለአለቆችም፥ ለዓለምም መዘባበቻ ሆነናልና።

[10] እኛስ ስለ ክርስቶስ ብለን አላዋቂዎች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ጠቢባን ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ ክቡራን ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን።

[11] እኛ እስከዚች ቀን ድረስ እንራባለን፤ እንጠማለን፤ እንራቈታለን፤ እንሰደዳለን፤ ማረፊያም የለንም፤ እንደበደባለንም።

[12] በእጃችን ሥራ እያገለገልን እንደክማለን፤ ይረግሙናል፤ እኛ ግን እንመርቃቸዋለን፤ ያሳድዱናል፤ እኛ ግን እንጸልይላቸዋለን፤ እንታገሣቸዋለንም።

[13] ይሰድቡናል፥ እንማልዳቸዋለን፤ በዓለም እንደ ጊጤ ሆን፤ በሁሉም ዘንድ የተናቅን ሆን።

[14] ይህንም የጻፍሁላችሁ ላሳፍራችሁ አይደለም፤ ልጆቼና ወዳጆቼ እንደ መሆናችሁ ልመክራችሁና ላስተምራችሁ ነው እንጂ፤ እኔ ለሁላችሁ ቤዛችሁ ነኝ፤ እናንተ ግን አላፈራችሁኝም።

[15] በክርስቶስ ብዙ መምህራን ቢኖሩአችሁም አባቶቻችሁ ብዙዎች አይደሉም፤ እኔ በኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርት ወልጄአችኋለሁና።

[16] ወንድሞቻችን ሆይ! እኔን እንድትመስሉ እማልዳችኋለሁ፤

[17] ስለዚህም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዳስተማርሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የሄድሁበትን መንገድ ይገልጥላችሁ ዘንድ በእግዚአብሔር የታመነና ልጄ ወዳጄ የሆነ ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ።

[18] እነሆ፥ ወደ እናንተ ስላልመጣሁ ከእናንተ ወገን የታበዩ ሰዎች አሉ።

[19] እንኪያስ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ፈጥኜ እመጣለሁ፤ ነገር ግን የትዕቢተኟችን ነገር አልሻም፤ ኀይላቸውን እሻለሁ እንጂ።

[20] የእግዚአብሔር መንግሥት በኀይል እንጂ በቃል አይደለምና።

[21] እንዴት ሆኜ ወደ እናንተ ልመጣ ትወዳላችሁ? በበትር ነውን? ወይስ በፍቅርና በቅንነት መንፈስ?

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 — Chapters