Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:40

[1] ወድሞቼ ሆይ፥ እኔስ የሥጋና የደም እንደ መሆናችሁ፥ ክርስቶስንም በማመን ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ እንደ መንፈሳውያን ላስተምራችሁ አልቻልሁም።

[2] ወተትን ጋትኋችሁ፤ ጽኑ መብልም ያበላኋችሁ አይደለም፤ ገና አልጠነከራችሁምና፤

[3] በሥጋዊ ሕግም ትኖራላችሁና እርስ በርሳችሁ የምትቃኑና የምትከራከሩ ከሆነ ግን ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? እንደ ሰው ልማድስ የምትኖሩ መሆናችሁ አይደለምን?

[4] ከመካከላችሁ ፥ “እኔ የጳውሎስ ነኝ ” የሚል አለና፤ ሌላውም ፥ “እኔ የአጵሎስ ነኝ ” ቢል እናንተ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን?

[5] እንግዲህ ጳውሎስ ምንድን ነው? አጵሎስስ ምንድን ነው? እነርሱስ በቃላቸው የአመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ሰጠው ነው።

[6] እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስም አጠጣ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አሳደገ።

[7] አሁንም የሚተክልም ቢሆን፥ የሚያጠጣም ቢሆን የሚጠቅመው ነገር የለም፤ የሚያሳድግ እግዚአብሔር ነው እንጂ።

[8] የሚተክልም፥ የሚያጠጣም አንድ ናቸው፤ ሁሉም እንደ ድካማቸው ዋጋቸውን ይቀበላሉ።

[9] በእግዚአብሔር ሥራ እንተባበራለንና፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ።

[10] እግዚአብሔር እንደ ሰጠኝ ጸጋ መጠን እንደ ብልህ የጠራቢዎች አለቃ ሆኜ እኔ መሠረት ጣልሁ፤ ሌላውም በእርሱ ላይ ያንጻል፤ እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንደሚያንጽ ይጠንቀቅ።

[11] ነገር ግን ከተመሠረተው በቀር ሌላ መሠረት ሊመሠርት የሚችል የለም፤ መሠረቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

[12] በዚህ መሠረት ላይ በወርቅና በብር፥ በከበረ ድንጋይና በእንጨት፥ በሣርና በአገዳ የሚያንጽ ቢኖርም፥

[13] የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጻል፤ እሳትም በፈተነው ጊዜ ቀኑ ይገልጠዋል፤ የእያንዳንዱንም ሥራ እሳት ይፈትነዋል።

[14] ሥራው ጸንቶ የተገኘለት ሰው ዋጋውን የሚቀበል እርሱ ነው።

[15] ሥራው የተቃጠለበት ግን ዋጋውን ያጣል፤ እርሱም ከእሳት እንደሚድን ሰው ይድናል።

[16] እናንተ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንፈስም በእናንተ ላይ አድሮ እንደሚኖር አታውቁምን?

[17] የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚያፈርሰውን ግን እርሱን ደግሞ እግዚአብሔር ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነውና፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም እናንተ ራሳችሁ ናችሁ፤ እንግዲያስ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አታርክሱ።

[18] ራሳችሁን አታስቱ፤ ከመካከላችሁ በዚህ ዓለም ጥበበኛ እንደ ሆነ የሚያስብ ሰው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ራሱን ዐላዋቂ ያድርግ።

[19] የዚህ ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ ድንቐርና ነውና፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና ፥ “ጠቢባንን የሚገታቸው ተንኰላቸው ነው።”

[20] ዳግመኛ “የጥበበኟች አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ያውቃል” ብሎአል።

[21] ስለዚህም እንግዲህ አንዱ ስንኳ በሰው አይመካ፤ ሁሉ የእናንተ ነውና።

[22] ጳውሎስም ቢሆን፥ አጵሎስም ቢሆን፥ ጴጥሮስም ቢሆን፥ ዓለምም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ ሞትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን ሁሉ የእናንተ ነው።

[23] እናንተ ግን የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 — Chapters