Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:34

[1] ለቅዱሳን ስለሚደረገው አስተዋፅኦ በገላትያ ላሉት ምእመናን እንደ ደነገግሁት እናንተም እንዲሁ አድርጉ።

[2] እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያንጊዜ እንዳይሆን፥ ከእናንተ ሰው ሁሉ በየሳምንቱ እሑድ የተቻለውን ያወጣጣ፤ ያገኘውንም በቤቱ ይጠብቅ።

[3] በመጣሁ ጊዜም ስጦታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሱ ዘንድ የመረጣችኋቸውን ሰዎች መልእክቴን ጨምሬ እልካቸዋለሁ።

[4] ለመሄድ ቢቻለኝ ግን እኔ ራሴ እሄዳለሁና፥ እነርሱም አብረውኝ ይሄዳሉ።

[5] መቄዶንያም ደርሼ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመቄዶንያ በኩል አልፋለሁና።

[6] እናንተም ወደምሄድበት ትሸኙኝ ዘንድ ምንአልባት የሆነውን ቀን ያህል በእናንተ ዘንድ እቈይ፥ ወይም እከርም ይሆናል።

[7] አሁን እግረ መንገዴን ላያችሁ አልሻም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የፈቀደ እንደ ሆነ የሆነውን ቀን ያህል በእናንተ ዘንድ እንደምቈይ ተስፋ አደርጋለሁ።

[8] እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቈያለሁ።

[9] ሥራ የሞላበት ታላቅ በር ተከፍቶልኛልና፤ ነገር ግን ብዙዎች ተቃዋሚዎች አሉ።

[10] ጢሞቴዎስም በመጣ ጊዜ በእናንተ ዘንድ ያለ ፍርሀት እንዲኖር ተጠንቀቁ፤ እንደ እኔ የእግዚአብሔርን ሥራ ይሠራልና።

[11] የሚንቀውም አይኑር፤ ከወንድሞቻችን ጋር እጠብቀዋለሁና፥ ወደ እኔ እንዲመጣ በሰላም ሸኙት።

[12] ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስም ከወንድሞች ጋር ወደ እናንተ እንዲመጣ መላልሼ ማልጄው ነበር፤ አሁን ሊመጣ አልወደደም፤ በተቻለው ጊዜ ግን ይመጣል።

[13] ትጉ፤ በሃይማኖትም ቁሙ፤ ታገሡ ጽኑ፤

[14] ሁሉን በፍቅር አድርጉ።

[15] ወንድሞቻችን ሆይ፥ የእስጢፋኖስና የፈርዶናጥስ፥ የአካይቆስም ቤተሰቦች፥ የአካይያ መጀመሪያዎች እንደ ሆኑ፥ ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቁ ዘንድ እማልዳችኋለሁ።

[16] እናንተም እንደ እነዚህ ላሉትና ከእኛ ጋር በሥራ ተባብሮ ለሚደክም ሁሉ ትታዘዙላቸው ዘንድ እማልዳችኋለሁ።

[17] እስጢፋኖስ፥ ፈርዶናጥስና አካይቆስ በመምጣታቸውም ደስ ይለኛል፤ እናንተ ያጐደላችሁትን እነርሱ ፈጽመዋልና።

[18] እነርሱ መንፈሴንና መንፈሳችሁን ደስ አሰኝተዋል፤ እንዲህ ያሉትንም ዕወቌቸው።

[19] በእስያ ያሉ ምእመናን ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ አቂላና ጵርስቅላ በቤታቸው ከእነርሱ ጋር ያሉ ምእመናንም ሁሉ በጌታችን እጅግ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

[20] ወንድሞቻችሁ ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ በተቀደሰች ሰላምታ እርስ በርሳችሁ ሰላም ተባባሉ።

[21] እኔ ጳውሎስ ይህን ሰላምታ በእጄ ጻፍሁ።

[22] ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወደው የተለየ ይሁን፤ ጌታችን ይመጣል።

[23] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋራ ይሁን።

[24] የእኔም ፍቅር በኢየሱስ ክርስቶስ ከእናንተ ጋር ይሁን። አሜን። በኤፌሶን ተጽፎ በጢሞቴዎስና በእስጢፋኖስ፥ በፈርዶናጥስና በአካይቆስ እጅ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች የተላከው መጀመሪያዉ መልእክት ተፈጸመ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 — Chapters