[1] በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን ከተጠራ ከጳውሎስና ከወንድማችን ከሶስቴንስ፥
[2] በቆሮንቶስ ሀገር ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለከበሩና ቅዱሳን ለተባሉ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ለሚጠሩ ሁሉ፥
[3] ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።
[4] ስለ እናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ ስለተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ።
[5] በአነጋገር ሁሉ፥ በዕውቀትም ሁሉ ከብራችሁበታልና።
[6] ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ እንደ ጸና መጠን።
[7] ፍጹማንም እንድትሆኑ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስንም መምጣት ተስፋ አድርጋችሁ ፍጹም ጸጋን እንዳታጡ፥
[8] እርሱም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነውር ትገኙ ዘንድ እስከ ፍጻሜ ያጸናችኋል።
[9] ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።
[10] ወንድሞቻችን! አንድ ቃል እንድትናገሩ፥ እንዳታዝኑ፥ ፍጹማንም እንድትሆኑ፥ ሁላችሁንም ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እማልዳችኋለሁ፤ እንዳትለያዩም አንድ ልብና አንድ አሳብ ሆናችሁ ኑሩ።
[11] ወንድሞቻችን ሆይ! እንደምትጣሉና እንደምትከራከሩ ከቀሎኤስ ወገኖች ስለ እናንተ ነገሩኝ።
[12] እነሆ፥ እርስ በርሳችሁ ፥ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ እኔ የአጵሎስ ነኝ፤ እኔ የኬፋ ነኝ፤ እኔ የክርስቶስ ነኝ ” የምትሉትን እነግራችኋለሁ።
[13] ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ወይስ በውኑ ጳውሎስ ስለ እናንተ ተሰቅሎአልን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠምቃችኋልን?
[14] ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ከእናንተ ወገን ሌላ ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ።
[15] በእርሱ ስም ተጠመቅን የሚል እንዳይኖር።
[16] ነገር ግን የእስጢፋኖስን ቤተ ሰብእ አጥምቄአለሁ፤ እንግዲህ ሌላም ያጠመቅሁት እንዳለ አላውቅም።
[17] ክርስቶስ ወንጌልን ለመስበክ እንጂ ለማጥመቅ አልላከኝምና፥ የክርስቶስን መስቀሉን ከንቱ እንዳናደርግ ነገርን በማራቀቅ አይደለም።
[18] የመስቀሉ ነገር በሚጠፉ ሰዎች ዘንድ ስንፍና ነውና፥ ለምንድነው ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው።
[19] መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና ፥ “እኔ የጥበበኟችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የመካሪዎችንም ምክር እንቃለሁ።”
[20] እንግዲህ ጥበበኛ ማን ነው? ጸሓፊስ ማን ነው? ይህን ዓለምስ የሚመረምረው ማን ነው? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ስንፍና አላደረገውምን?
[21] ሰዎች በጥበባቸው በማያውቁት በእግዚአብሔር ጥበብ ስንፍና በሚመስላቸው ትምህርት ያመኑትን ሊያድናቸው እግዚአብሔር ወድዶአልና።
[22] አይሁድ ምልክትን ይጠይቃሉ፤ የጽርዕ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ።
[23] እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ስንፍና ነው።
[24] ለእኛ ለዳንነው ግን ከአይሁድ፥ ከአረሚም ብንሆን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው።
[25] የእግዚአብሔር ስንፍና ከሰው ይልቅ ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።
[26] ወንድሞቻችን! እንግዲህ እንዴት እንደ ተጠራችሁ እዩ፤ በሥጋ እጅግ ብዙዎች ዐዋቂዎች አይደላችሁምና፥ ብዙዎች ኀያላንም አይደላችሁምና፥ በዘመድም ብዙዎች ደጋጎች አይደላችሁምና።
[27] ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኟችን ሊያሳፍር የዚህን ዓለም ሰነፎች መረጠ፤ ኀይለኟችንም ያሳፍር ዘንድ እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ደካሞች መረጠ።
[28] አለን የሚሉትንም ያሳፍር ዘንድ ዘመድ የሌላቸውንና የተናቁትን፥ ከቐጥርም ያልገቡትን እግዚአብሔር መረጠ።
[29] ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ።
[30] እናንተም በኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ናችሁ፤ በእርሱም ከእግዚአብሔር ጥበብንና ጽድቅን፥ ቅድስናንና ቤዛነትን አገኘን።
[31] መጽሐፍ እንደ አለው ይሆን ዘንድ “የሚመካስ በእግዚአብሔር ይመካ።”