[1] ወደ ታንኳም ወጥቶ ተሻገረና ወደ ከተማው ደረሰ።
[2] እነሆም፥ አንድ መፃጕuዕ በአልጋ ተሸክመው ወደ እርሱ አመጡ፤ ጌታችን ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ መፃጒዑን ፥ “ልጄ ሆይ፥ ጽና፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሀል ” አለው።
[3] እነሆም፥ ከጻፎች ወገን ሰምተው በልባቸው ፥ “ይህስ ይሳደባል ” ተባባሉ።
[4] ጌታችን ኢየሱስም አሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው ፥ “በልባችሁ ለምን ክፉ ነገር ታስባላችሁ?
[5] ኀጢአትህ ተሰረየልህ ከማለትና ተነሥተህ ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?
[6] ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ” ከዚህ በኋላ ያን መፃጒዕ ፥ “ተነሥ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ ” አለው።
[7] ተነሥቶም አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ሄደ።
[8] ሕዝቡም አይተው አደነቁ፤ እንዲህ ያለውን ሥልጣን ለሰው የሰጠ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
[9] ጌታችን ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ስሙ ማቴዎስ የተባለ ሰው በቀረጥ መቀበያው ተቀምጦ አገኘና ፥ “ተከተለኝ ” አለው፤ ተነሥቶም ተከተለው።
[10] በቤቱም ለምሳ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኀጢአተኟች መጥተው ከጌታችን ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ።
[11] ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን ፥ “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኀጢአተኟች ጋር ለምን ይበላል?” አሉአቸው።
[12] ጌታችን ኢየሱስም ሰምቶ እንዲህ አላቸው ፥ “በሽተኟች ባለ መድኀኒትን ይሹታል፤ ጤነኟች ግን አይሹትም።
[13] ሂዱ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እመርጣለሁ ያለው ምን እንደ ሆነ ዕወቁ፤ ኃጥኣንን እንጂ፥ ጻድቃንን ወደ ንስሓ ልጠራ አልመጣሁምና።”
[14] ከዚህ በኋላ፥ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ መጥተው ፥ “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ እንጿማለን፤ ደቀ መዛሙርትህስ ለምን አይጿሙም?” አሉት።
[15] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ አይችሉም፤ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል። ያንጊዜ ይጿማሉ።
[16] የአዲስ ልብስ ዕራፊም በአሮጌ ልብስ ቀዳዳ ላይ የሚጥፍ የለም፤ ደኅነኛውን ልብስ ይዞት ይሄዳልና፤ ቀዳዳውንም ያሰፋዋልና።
[17] በአሮጌ ረዋት አዲስ የወይን ጠጅ አይጨምሩም፤ ቢጨመር ግን ረዋቱ ይቀደዳል፤ ወይኑም ይፈስሳል፤ ረዋቱም ይቀደዳል፤ ነገር ግን፤ አዲሱን ወይን በአዲስ ረዋት ይሾሙታል፤ ሁለቱም እርስ በርሳቸው ይጠባበቃሉ።”
[18] ይህንም ሲነግራቸው እነሆ፥ አንድ መኰንን መጥቶ ፥ “ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፤ ትድናለችም ” እያለ ሰገደለት።
[19] ጌታችን ኢየሱስም ተነሥቶ ተከተለው፤ ደቀ መዛሙርቱም አብረውት ነበሩ።
[20] እነሆ፥ ከዐሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም ይፈስሳት የነበረች ሴት በኋላው መጥታ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች።
[21] በልቧ ፥ “የልብሱን ጫፍ ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ” ብላ ነበርና።
[22] ጌታችን ኢየሱስም መለስ ብሎ አያትና ፥ “ልጄ ጽኚ፤ እምነትሽ አዳነችሽ ” አላት፤ ከዚያም ሰዓት ጀምሮ ያቺ ሴት ዳነች።
[23] ጌታችን ኢየሱስም ወደዚያ መኰንን ቤት በደረሰ ጊዜ፥ አስለቃሾችንና የሚንጫጩትን ሰዎች አየ።
[24] “ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ የሞተች አይደለምና ፈቀቅ በሉ ” አላቸው፤ እነርሱም ሳቁበት።
[25] ሰዎቹ ከወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ ብላቴናዪቱም ተነሣች።
[26] የተአምራቱም ዝና በሀገሩ ሁሉ ተሰማ።
[27] ጌታችን ኢየሱስም ከዚያ በአለፈ ጊዜ ሁለት ዕውራን ፥ “የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ራራልን ” ብለው እየጮኹ ተከተሉት።
[28] ወደ ቤትም በገባ ጊዜ እነዚያ ዕውራን ወደ እርሱ መጡ፤ ጌታችን ኢየሱስም “ይህን ማድረግ እንዲቻለኝ ታምናላችሁን?” አላቸው፤ እነርሱም ፥ “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉት።
[29] “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ” ብሎ ዐይኖቻቸውን ዳሰሳቸው።
[30] ያንጊዜም ዐይኖቻቸው ተገለጡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ ” ብሎ አዘዛቸው።
[31] እነርሱ ግን፥ ወጥተው በዚያ ሀገር ሁሉ ስለእርሱ ተናገሩ።
[32] እነዚያም ከወጡ በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ወደ እርሱ አመጡ።
[33] ያደረበትም ጋኔን በወጣ ጊዜ ዲዳ የነበረው ተናገረ፤ ሰዎችም “በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ያለ ከቶ አልታየም ” እያሉ አደነቁ።
[34] ፈሪሳውያን ግን “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ” አሉ።
[35] ጌታችን ኢየሱስም በምኵuራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥት ወንጌልንም እየሰበከ፥ በሕዝቡም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በየከተማውና በየመንደሩ ሁሉ ተመላለሰ።
[36] ብዙ ሰዎችንም አይቶ አዘነላቸው፤ ደክመው ነበሩና፥ እረኛ እንደሌላቸው በጎችም ተበትነው ነበርና። ዘካ.
[37] ያንጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “መከሩስ ብዙ ነው፤ ሠራተኛው ግን ጥቂት ነው።
[38] እንግዲህ ለመከሩ ሠራተኛን ይጨምር ዘንድ የመከሩን ባለቤት ለምኑት።”