Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 7:39

[1] ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ፥ ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ።

[2] እንዲህም አላቸው፤ “በፊታችሁ ወደ አለችው መንደር ሂዱ፤ ያንጊዜም የታሰረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ።

[3] ምን ታደርጋላችሁ? የሚላችሁ ቢኖርም ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ፥ ያንጊዜ ይሰዱአችኋል።”

[4] ይህም ሁሉ የሆነው በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው።

[5] “ለጽዮን ልጅ ፥ እነሆ፥ የዋህ ንጉሥሽ በአህያይቱና በአህያይቱ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት”።

[6] ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ጌታችን ኢየሱስ እንደ አዘዛቸው አደረጉ።

[7] አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በላያቸው ጫኑ፤ ጌታችን ኢየሱስም በእነርሱ ላይ ተቀመጠ።

[8] ብዙ ሕዝብም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፎች ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር።

[9] በፊቱ የሚሄዱትና የሚከተሉት ሕዝብም ፥ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም ” እያሉ ይጮሁ ነበር።

[10] ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ፥ “ከተማዪቱ ይህ ማነው?” እያለች ታወከች።

[11] ሕዝቡም ፥ “ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው ” አሉ።

[12] ጌታችን ኢየሱስም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም መደርደሪያ፥ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ።

[13] “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል ተብሎ ተጽፎአል እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት ” አላቸው።

[14] በቤተ መቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡ፤ አዳናቸውም።

[15] ያንጊዜም የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ተአምራት፥ ልጆችንም በቤተ መቅደስ ፥ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ ” እያሉ ሲጮሁ ባዩ ጊዜ ደስ አላላቸውም።

[16] እነርሱም ፥ “እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን?” አሉት፤ ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አዎን፥ እሰማለሁ፥ ‘ከልጆችና ከሕፃናት አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህ ’ የሚለውን ቃል ከቶ ያነበባችሁበት ጊዜ የለምን?” አላቸው።

[17] ትቶአቸውም ከከተማው ወደ ቢታንያ ሄደ፤ በዚያም አደረ።

[18] በነጋም ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ።

[19] በመንገድም አጠገብ የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል ብቻ በቀር ምንም ፍሬ አላገኘባትም፤ “እንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይኑርብሽ ” አላት፤ ያንጊዜውንም በለሲቱ ደረቀች።

[20] ደቀ መዛሙርቱም አይተው “ይህቺ በለስ እንዴት ወዲያውኑ ደረቀች?” ብለው አደነቁ።

[21] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እላችኋለሁ እምነት ቢኖራችሁ፥ ባትጠራጠሩም በበለሲቱ እንደ ተደረገው ብቻ የምታደርጉ አይደለም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይደረግላችኋል።

[22] አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ።”

[23] ወደ ቤተ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር፥ የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች፥ ወደ እርሱ መጥተው ፥ “በማን ሥልጣን ይህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት።

[24] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “እኔም አንዲት ቃል እጠይቃችኋለሁ፤ የነገራችሁኝ እንደ ሆነ እኔም በምን ሥልጣን ይህን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ ” አላቸው።

[25] “የዮሐንስ ጥምቀቱ ከየት ነው? ከሰማይ ነውን? ወይስ ከሰው?” አላቸው፤ እርስ በርሳቸውም ተነጋግረው እንዲህ አሉ ፥ “ከሰማይ ነው ብንለው እንኪያ ለምን አላመናችሁበትም? ይለናል።

[26] ከሰው ነው ብንለውም ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራቸዋለን፤”

[27] እነርሱም ፥ “አናውቅም ” ብለው መለሱለት፤ እርሱም ፥ “እንኪያስ እኔም በምን ሥልጣን ይህን እንደማደርግ አልነግራችሁም ” አላቸው።

[28] “ምን ትላላችሁ? አንድ ሰው ሁለት ወንድማማች ልጆች ነበሩት፤ ታላቁንም ፥ ልጄ ሆይ! ዛሬ ወደ ወይኔ ቦታ ሂድና ሥራ አለው።

[29] ልጁም መልሶ እንቢ አለ፤ ኋላ ግን ተጸጽቶ ሄደ።

[30] ሁለተኛውንም እንዲሁ አለው፤ እርሱም እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም።

[31] እንግዲህ ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመ ማንኛው ነው?” አላቸው፤ “ፊተኛው ነዋ ” አሉት፤ ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና አመንዝሮች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል።

[32] ዮሐንስ በጽድቅ ጎዳና ወደ እናንተ መጣ፤ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና አመንዝሮች ግን አመኑበት፤ እናንተም በኋላ በእርሱ ለማመን አይታችሁ እንኳ ንስሓ አልገባችሁም።

[33] “ሌላ ምሳሌ ስሙ፤ ባለቤት ሰው ወይንን ተከለ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፤ መጭመቂያም አስቈፈረለት፤ ግንብም ሠራለት፤ ለገባሮችም ሰጥቶአቸው ሄደ።

[34] የሚያፈራበት ወራት በደረሰ ጊዜም፥ ከወይኑ ፍሬ ያመጡለት ዘንድ አገልጋዮችን ወደ ገባሮቹ ላከ።

[35] ገባሮቹም አገልጋዮቹን ይዘው፥ አንዱን በበትር ደበደቡት፤ አንዱንም ገደሉት፤ ሌላውንም በድንጋይ መቱት።

[36] ከዚያም በኋላ ከቀደሙት የሚበዙ ሌሎች አገልጋዮችን ላከ፤ እነርሱንም እንዲሁ አደረጉባቸው።

[37] በኋላም ልጄንስ ይፈሩት ይሆናል ብሎ ልጁን ላከ።

[38] ገባሮቹም ልጁን ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው ፥ እነሆ፥ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ ተባባሉ።

[39] ይዘውም ከወይኑ ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት።

[40] እንግዲህ የወይኑ ቦታ ባለቤት በመጣ ጊዜ እነዚህን ገባሮች ምን ያደርጋቸዋል?”

[41] እነርሱም ፥ “ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፤ ወይኑንም በየጊዜው ፍሬውን ለሚሰጡት ለሌሎች ገባሮች ይሰጣል ” አሉት።

[42] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “በመጻሕፍት ያለውን ያነበባችሁበት ጊዜ የለምን? ግንበኟች የናቁአት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ሆነች፤ ይህቺም ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ናት።

[43] ስለዚህም እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች፤ ፍሬዋንም ለሚያደርጉ ለአሕዛብ ትሰጣለች።

[44] በዚያችም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ በላዩ የምትወድቅበትንም ትፈጨዋለች።”

[45] የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ፥ ስለ እነርሱ እንደተናገረ ዐወቁ።

[46] ሊይዙትም ሲፈልጉ ሕዝቡን ፈሩአቸው፤ በእነርሱ ዘንድ እንደ ነቢይ ነበርና።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters