Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:23

[1] በዚያ ወራትም የገሊላው ንጉሥ ሄሮድስ የጌታችን የኢየሱስን ዝና ሰማ።

[2] ሎሌዎቹንም ፥ “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶአል፤ ስለዚህ በእርሱ ተአምራት ይደረጋል ” አላቸው።

[3] እርሱ ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት፥ ዮሐንስን አሲዞ በእስር ቤት አግዞት ነበርና።

[4] ዮሐንስም “እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አይገባህም ” ይለው ነበር።

[5] ሊገድለውም ወዶ ሳለ ሕዝቡን ይፈራቸው ነበር፤ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ያዩት ነበርና።

[6] የሄሮድስም የልደቱ ቀን በሆነ ጊዜ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነችለት፤ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው።

[7] ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ ሊሰጣት ማለላት።

[8] እርስዋ ግን አስቀድማ በእናቷ ዘንድ ዐውቃ ነበርና “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አሁን በወጭት ስጠኝ” አለችው።

[9] ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው፥ አብረውት በማዕዱ ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች ይሰጧት ዘንድ አዘዘ።

[10] ልኮም በግዞት በእስር ቤት ሳለ የዮሐንስን ራስ አስቈረጠው።

[11] ራሱንም በወጭት አምጥተው ለዚያች ብላቴና ሰጡአት፤ እርስዋም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች።

[12] ደቀ መዛሙርቱም መጡ፤ በድኑንም ወስደው ቀበሩት፤ መጥተውም ለጌታ ለኢየሱስ ነገሩት።

[13] ጌታችን ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ በታንኳ ሆኖ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከየመንደሩ በእግር ተከተሉት።

[14] በወጣም ጊዜ ብዙ ሰዎችን አይቶ አዘነላቸው፤ ድውዮቻቸውንም አዳነላቸው።

[15] በመሸ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው ፥ “ቦታው ምድረ በዳ ነው፤ ሰዓቱም አልፎአል፤ ወደ መንደር ገብተው ምግባቸውን ይገዙ ዘንድ ሕዝቡን አሰናብታቸው ” አሉት።

[16] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እንደ ራባቸው ሊሄዱ አይገባም፤ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ” አላቸው።

[17] እነርሱም “ከሁለት ዓሣና ከአምስት እንጀራ በቀር፥ በዚህ ምንም የለንም ” አሉት።

[18] እርሱም “እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ ” አላቸው።

[19] በመስኩም ላይ እንዲቀመጡ ሰዎችን አዘዘ፤ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ተመለከተና ባርኮ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ አቀረቡ።

[20] ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቊርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ።

[21] የበሉትም፥ ከሴቶችና ከልጆች በቀር ወንዶቹ አምስት ሺህ ያህሉ ነበር።

[22] ያንጊዜም ሕዝቡን እስኪያሰናብት ድረስ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳው ገብተው ወደ ባሕር ማዶ ቀድመውት ይሄዱ ዘንድ ግድ አላቸው።

[23] ከዚያም በኋላ ሕዝቡን አሰናብቶ ሊጸልይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ፤ በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር።

[24] ታንኳው ግን እነሆ፥ በባሕር መካከል ነበር፤ ከማዕበሉም የተነሣ ይታወክ ነበር፤ ነፋስ ከፊቱ ነበርና።

[25] ከሌሊቱም በአራተኛዪቱ ክፍለ ሰዓት ጌታችን ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ።

[26] ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ፥ “ምትሐት ነው ” ብለው ደነገጡ፤ ከፍርሀትም የተነሣ ጮኹ።

[27] ወዲያውም ጌታችን ኢየሱስ ፥ “አይዞአችሁ፥እኔ ነኝ አትፍሩ ” አላቸው።

[28] ጴጥሮስም መልሶ ፥ “አቤቱ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ ” አለው፤

[29] እርሱም ፥ “ና ” አለው። ጴጥሮስም ከታንኳው ወርዶ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ።

[30] ነገር ግን ነፋሱ በርትቶ ባየ ጊዜ ፈራ፤ ሊሰጥምም ጀመረ፥ ያንጊዜም “አቤቱ፥ አድነኝ ” ብሎ ጮኸ

[31] ወዲያው ጌታችን ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና ፥ “አንተ እምነት የጐደለህ ለምን ተጠራጠርህ?” አለው።

[32] ወደ ታንኳውም በወጣ ጊዜ ወዲያውኑ ነፋሱ ፀጥ አለ።

[33] በታንኳውም ውስጥ የነበሩት ሁሉ “በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ” እያሉ ሰገዱለት።

[34] ባሕሩንም ተሻግረው ወደ ጌንሴሬጥ ምድር ደረሱ።

[35] የዚያ ሀገር ሰዎችም ዐወቁት፤ ወደ አውራጃዎቻቸውም ሁሉ ላኩ፤ በሽተኟችንም ሁሉ አመጡለት።

[36] የልብሱንም ዘርፍ ይዳስሱ ዘንድ ለመኑት፤ የዳሰሱትም ሁሉ ይድኑ ነበር።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters