Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 8:44

[1] በዚያችም ቀን ጌታችን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ።

[2] ወደ ታንኳም ወጥቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበሩ።

[3] እንዲህ እያለም በምሳሌ ብዙ ነገርን ነገራቸው፤ “እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ።

[4] ሲዘራም በመንገድ የወደቀ ዘር ነበረ፤ የሰማይ ወፎችም መጥተው በሉት።

[5] ብዙ አፈር በሌለበት ጭንጫ ላይ የወደቀ ዘርም ነበረ፤ ለመሬቱም ጥልቀት አልነበረውምና ወዲያውኑ በቀለ።

[6] ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥርም አልነበረውምና ደረቀ።

[7] በእሾኽ መካከልም የወደቀ ዘር ነበረ፤ በበቀለም ጊዜ እሾኽ አነቀው፤ አጣበቀውም።

[8] በመልካም ምድር ላይም የወደቀ ዘር ነበረ፤ ፍሬም ሰጠ፤ መቶ ያፈራ ነበረ፤ ስድሳም ያፈራ ነበረ፤ ሠላሳም ያፈራ ነበረ።

[9] ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ።”

[10] ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ስለምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት።

[11] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም።

[12] ላለው ይሰጡታል፤ ይጨምሩለታልም፤ የሌለውን ግን ያንኑ ያለውን ቅሉ ይወስዱበታል።

[13] ስለዚህም እያዩ ስለማያዩ፥ እየሰሙም ስለማይሰሙ፥ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ።

[14] መስማትን ትሰማላችሁ፤ ልብ አታደርጉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ አትመለከቱም።

[15] በዐይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው የዚህ ሕዝብ ልቡ ደንድኖአልና፥ ጆሮአቸውም ደንቐሮአል፤ ዐይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸም ዘንድ።

[16] የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ያያሉና፥ ጆሮዎቻችሁም ይሰማሉና ብፁዓት ናቸው።

[17] እውነት እላችኋለሁ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም።

[18] “እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ።

[19] የመንግሥተ ሰማያትን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው መጥቶ በልቡ የተዘራውን ቃል ይነጥቀዋል፤ በመንገድ የተዘራው ዘር ይህ ነው።

[20] በጭንጫ ላይ የተዘራውም ቃሉን የሚሰማና ፈጥኖ በደስታ የሚቀበለው ነው።

[21] ነገር ግን፥ ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ላይ ሥር የለውም፤ በቃሉም ምክንያት መከራ፥ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይክዳል።

[22] በእሾኽ መካከል የተዘራውም ቃሉን ሰምቶ የዚህ ዓለም አሳብና የሀብት ማታለል ቃሉን አንቆት ያለ ፍሬ የሚቀረው ነው።

[23] ነገር ግን በመልካም ምድር ላይ የተዘራው ይህ ቃሉን የሚሰማና የሚያስተውል ነው፤ እርሱም አንዱ መቶ፥ ሌላውም ስድሳ፥ ሌላውም ሠላሳ ፍሬ ይሰጣል።”

[24] ሌላ ምሳሌም እንዲህ ሲል መሰለላቸው፤ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ መልካም ዘርን የዘራ ሰውን ትመስላለች።

[25] ቤተሰቦቹም ተኝተው ሳለ፥ ጠላት መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ።

[26] ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ፥ ወዲያውኑ እንክርዳዱ ታየ።

[27] የባለ እርሻው አገልጋዮችም መጥተው አቤቱ በእርሻህ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? እንግዲህ እንክርዳዱ ከየት መጣ? አሉት።

[28] እርሱም ጠላት ሰው ይህን አደረገ አላቸው፤ አገልጋዮቹ ግን ፥ እንግዲህ ሂደን ልናርመው ትወዳለህን? አሉት።

[29] እንክርዳዱን ስታርሙ ስንዴውንም ጨምራችሁ እንዳትነቅሉ አይሆንም፤

[30] ተዉአቸው እስከ መከር ድረስ አብረው ይደጉ፤ በመከርም ጊዜ አጫጆችን አስቀድማችሁ እንክርዳዱን ልቀሙ፤ በየነዶውም አስራችሁ በእሳት አቃጥሉት፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ሰብስቡት እላቸዋለሁ ” አለ።

[31] ሌላም ምሳሌ እንዲህ ብሎ መሰለላቸው፤ “መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው ላይ የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች።

[32] እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በአደገች ጊዜ ግን ከአታክልት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም መጥተው ከቅርንጫፎችዋ በታች እስኪያርፉ ድረስ ታላቅ ዛፍ ትሆናለች።”

[33] ሌላ ምሳሌንም ነገራቸው፤ እንዲህም አለ ፥ “መንግሥተ ሰማያት ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የለወሰችውን፥ ሁሉንም እንዲቦካ ያደረገውን እርሾ ትመስላለች።”

[34] ጌታችን ኢየሱስም ይህን ሁሉ ለሕዝቡ በምሳሌ ነገራቸው፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም።

[35] በነቢይ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከጥንት የተነገረውንም ምሳሌ እናገራለሁ” የተባለው ይፈጸም ዘንድ።

[36] ከዚህም በኋላ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጒምልን ” አሉት።

[37] እርሱም መልሶ አላቸው፤ “መልካም ዘርን የዘራ የሰው ልጅ ነው።

[38] እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው።

[39] የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም ፍጻሜ ነው፤ አጫጆቹም መላእክት ናቸው።

[40] እንግዲህ አስቀድሞ እንክርዳዱን እንደሚለቅሙት፥ በእሳትም እንደሚያቃጥሉት በዚህ ዓለም ፍጻሜም እንዲሁ ይሆናል።

[41] የሰው ልጅም መላእክቱን ይልካል፤ ከመንግሥቱም ዐላውያንንና በደልን የሚያደርጉትን ሁሉ ይሰበስባሉ።

[42] ወደ እሳት ጒድጓድም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

[43] ያንጊዜም ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ፤ ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ።

[44] “ዳግመኛም መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተቀበረች ወርቅን ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወራት፤ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያችን እርሻ ገዛት።

[45] “ዳግመኛም መንግሥተ ሰማያት ክቡር ዕንቊን የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች።

[46] ዋጋዋም ብዙ የሆነ አንዲት ዕንቐን በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።

[47] ዳግመኛም መንግሥተ ሰማያት በባሕር ውስጥ የተጣለችውን፥ የዓሣ ወገንን ሁሉ የሰበሰበችውን መረብ ትመስላለች።

[48] በሞላችም ጊዜ ወደ ዳር አወጡአት፤ ተቀምጠውም መልካም መልካሙን መርጠው ወደ ሣጥናቸው ጨመሩ፤ መጥፎውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት።

[49] በዓለም ፍጻሜም እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት ይመጣሉ፤ ኃጥኣንንም ከጻድቃን መካከል ይለያሉ።

[50] ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወደ አለበት ወደ እሳት ጒድጓድም ይጥሉአቸዋል።”

[51] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እንግዲህ ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው፤ እነርሱም ፥ “አዎ፥ ጌታ ሆይ፥” አሉት።

[52] እርሱም ፥ “ስለዚህ ለመንግሥተ ሰማያት የሚያገለግል ጸሓፊ ሁሉ ከሣጥኑ አሮጌውንና ሐዲሱን የሚያወጣ ባለጸጋ ሰውን ይመስላል ” አላቸው።

[53] ጌታችን ኢየሱስም እነዚህን ምሳሌዎች በፈጸመ ጊዜ ከዚያ ሄደ።

[54] ወደ ሀገሩም መጣ፤ እስኪደነቁ ድረስም በምኲራባቸው አስተማራቸው፤ እንዲህም ይሉ ነበር፤ “እንግዲህ ይህ ሁሉ ጥበብና ተአምር ከየት ተሰጠው?

[55] ይህ የጠራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? የእናቱ ስምስ ማርያም አይደለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ፥ ስምዖንም፥ ይሁዳም አይደሉምን?

[56] እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደለምን? እንግዲህ ይህ ሁሉ ጥበብና ተአምር ከየት ተሰጠው?” እያሉ ስለ እርሱ ያንጐራጒሩ ጀመር።

[57] ጌታችን ኢየሱስ ግን “ነቢይ በሀገሩና በወገኑ እንጂ፥ በሌላ የማይከብርበት የለም ” አላቸው።

[58] ባለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራትን አላደረገም።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters