[1] በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በይሁዳ ክፍል በቤተ ልሔም ጌታችን ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
[2] እንዲህ ሲሉ ፥ “ኮከቡን በምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናልና፥ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?”
[3] ንጉሥ ሄሮድስም በሰማ ጊዜ ደነገጠ፤ ኢየሩሳሌምም በመላዋ ከእርሱ ጋር ደነገጠች።
[4] የካህናት አለቆችንና የሕዝቡን ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ “ክርስቶስ በየት ይወለዳል?” ብሎ ጠየቃቸው።
[5] እንዲህም አሉት፤ “በይሁዳ ክፍል በቤተ ልሔም ነው፤ በነቢይ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና።
[6] የይሁዳ ምድር አንቺ ቤተ ልሔም ከይሁዳ አለቆች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና።”
[7] ከዚህም በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠራቸው፤ ኮከቡ የታየበትንም ዘመን ከእነርሱ ተረዳ።
[8] “ሂዳችሁ የዚያን ሕፃን ነገር ርግጡን መርምሩ፤ ያገኛችሁትም እንደ ሆነ እኔም መጥቼ እሰግድለት ዘንድ በእኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ ” ብሎ ወደ ቤተ ልሔም ሰደዳቸው።
[9] እነርሱም ከንጉሡ ሰምተው ሄዱ፤ እነሆ፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ በአለበት ቦታ ላይ ደርሶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር።
[10] ኮከቡንም አይተው ታላቅ ደስታ ደስ አላቸው።
[11] ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አገኙት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው ወርቅና ዕጣን፥ ከርቤም፥ እጅ መንሻ አቀረቡለት።
[12] ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ነገራቸው፤ በሌላ መንገድም ወደ ሀገራቸው ሄዱ።
[13] እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ ፥ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ምድረ ግብፅ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ኑር ” አለው፤
[14] እርሱም በሌሊት ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ።
[15] ከእግዚአብሔር ዘንድ “ልጄን ከግብፅ ጠራሁት ” ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ፤ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።
[16] ከዚህም በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተዘባበቱበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቈጣና ጭፍራዎቹን ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን ልክ ሁለት ዓመት የሆናቸውን፥ ከዚያም የሚያንሱትን፥ በቤተ ልሔምና በአውራጃዎችዋ ሁሉ የነበሩትን ሕፃናት አስገደለ።
[17] ያን ጊዜ፥ በነቢዩ በኤርምያስ የተነገረው ተፈጸመ፤ እንዲህ ሲል ፥
[18] “ራሔል ስለ ልጆችዋ ስታለቅስ ብዙ ልቅሶና ዋይታ በራማ ተሰማ፤ መጽናናትንም እንቢ አለች፤ ልጆችዋ የሉምና።”
[19] ሄሮድስም በሞተ ጊዜ እነሆ፥ የእግዚአብሔር መልአክ በግብፅ ሀገር ለዮሴፍ በሕልም ታየው።
[20] እንዲህ ሲል ፥ “የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና፥ ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ።”
[21] እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ።
[22] አርኬላኦስም በአባቱ በሄሮድስ ፋንታ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ ለመሄድ ፈራ፤ በሕልምም ተገልጦለት ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ።
[23] በነቢያት “ልጄ ናዝራዊ ይባላል ” የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።