Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:24

[1] በዚያችም ሰዓት የጌታችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ፥ “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማነው?” እያሉ ወደ እርሱ ቀረቡ።

[2] ሕፃንንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመው።

[3] እንዲህም አለ ፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ ካልተመለሳችሁ፥ እንደዚህም ሕፃን ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።

[4] እንደዚህም ሕፃን ራሱን ዝቅ ያደረገ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ ይህ ነው።

[5] እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል።

[6] በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን የሚያሰናክል አህያ የሚፈጭበት ወፍጮ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም ይሻለዋል።

[7] “ከሚመጣው ማሰናከያ የተነሣ ለዓለም ወዮለት፤ ማሰናከያ ግድ ይመጣልና፤ ነገር ግን ማሰናከያን ለሚያመጣት ለዚያ ሰው ወዮለት።

[8] እጅህ ወይም እግርህ ብታስትህ ከአንተ ቈርጠህ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘለዓለም እሳት ከምትጣል፥ አንካሳ ወይም ጕuንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃልና።

[9] ዐይንህ ብታስትህ ከአንተ አውጥተህ ጣላት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ዘለዓለም ገሃነመ እሳት ከምትጣል፥ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃልና።

[10] “ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ስንኳ እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ሁልጊዜ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ።

[11] የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና።

[12] ምን ትላላችሁ? መቶ በጎች ያሉት ሰው ቢኖር፥ ከመካከላቸውም አንዱ ቢጠፋው፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ ይሄድ የለምን?

[13] እውነት እላችኋለሁ፤ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ ስለ ተገኘው ፈጽሞ ደስ ይለዋል።

[14] እንዲሁም ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንኳ ይጠፋ ዘንድ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት አይፈቀድም።

[15] “ወንድምህ አንተን ቢበድልህ፥ ሄደህ ብቻህን ሆነህ፥ ብቻውን አድርገህ ምከረው፤ ቢሰማህ ወንድምህን ጠቀምኸው።

[16] ባይሰማህ ግን በሁለተኛው ጊዜ ከአንተ ጋር አንድ ወይም ሁለት ምስክር ያዝ፤ ነገር ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር ቃል ይጸናልና።

[17] እነርሱን ባይሰማቸው ግን ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማት እንደ አረማዊና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።

[18] እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈቱት በሰማይ የተፈታ ይሆናል።

[19] ዳግመኛም እላችኋለሁ፤ ከእናንተ ሁለቱ በምድር ላይ ስለሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢተባበሩ፥ በሰማያት ባለው አባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል።

[20] ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት እኔ በዚያ በመካከላቸው እኖራለሁና።”

[21] ከዚህም በኋላ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ ፥ “አቤቱ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው።

[22] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ፥ “ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት ነው እንጂ እስከ ሰባት አልልህም።

[23] “ስለዚህም መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቈጣጠራቸው የወደደ ንጉሥን ትመስላለች።

[24] ሊቈጣጠራቸውም በጀመረ ጊዜ እልፍ መክሊት የሚከፍለውን አንድ ባለ ዕዳ ወደ እርሱ አመጡ።

[25] የሚከፍለውም ባጣ ጊዜ ጌታው እርሱና ሚስቱ፥ ልጆቹም፥ ያለውም ሁሉ እንዲሸጡና ዕዳውን እንዲከፍል አዘዘ።

[26] ወዲያውም ያ አገልጋይ ወድቆ ሰገደለት ፥ አቤቱ፥ ታገሠኝ፤ ሁሉን እከፍልሃለሁ እያለ ለመነው።

[27] ጌታውም ያን አገልጋይ አዘነለትና ፈታው፤ ዕዳውንም ተወለት።

[28] ነገር ግን ያ አገልጋይ በወጣ ጊዜ፥ ከአገልጋዮች ባልንጀሮቹ መቶ ዲናር የሚከፍለውን አንድ ባለ ዕዳ አገኘና የምትከፍለኝን ስጠኝ ብሎ አንቆ ያዘው።

[29] ያም የጌታው አገልጋይ እግሩ ላይ ወድቆ ፥ ታገሠኝ ሁሉንም እከፍልሃለሁ እያለ ለመነው።

[30] እርሱም እንቢ አለው፤ ዕዳውንም እስኪከፍለው ድረስ ወስዶ አሰረው።

[31] ባልንጀሮቹ አገልጋዮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት።

[32] ከዚህም በኋላ ጌታው ጠራውና እንዲህ አለው ፥ አንተ ክፉ አገልጋይ ስለ ለመንኸኝ ዕዳህን ሁሉ ተውሁልህ።

[33] አንተስ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህምን?

[34] ጌታውም ተቈጥቶ ዕዳውን ሁሉ ጨርሶ እስኪከፍለው ድረስ ለሚያሠቃዩት አሳልፎ ሰጠው።

[35] እናንተም የወንድሞቻችሁን በደል ከልባችሁ ይቅር ባትሉ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንዲሁ ያደርግባችኋል።”

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters