Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:52

[1] ከዚህ በኋላ ከኢየሩሳሌም የመጡ ጻፎችና ፈሪሳውያን ወደ ጌታችን ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ አሉ ፥

[2] “ደቀ መዛሙርትህ የሽማግሌዎችን ሥርዐት ለምን ይተላለፋሉ? እንጀራ በሚበሉበት ጊዜ እጃቸውን አይታጠቡምና።”

[3] እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው “እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ?

[4] እግዚአብሔርስ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ በአባቱና በእናቱ ላይ ክፉ ቃልን የተናገረ ፈጽሞ ይሙት ’ ብሏል።

[5] እናንተ ግን አባቱን ወይም እናቱን ከእኔ የምትጠቀምበት መባ ነው የሚል ሁሉ አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ።

[6] ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ።

[7] እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ በእናንተ ላይ እንዲህ ሲል መልካም ተናገረ ፥

[8] ‘ይህ ሕዝብ በከንፈራቸው ያከብሩኛል፤ በልባቸው ግን ከእኔ እጅግ ይርቃሉ።’

[9] የሰው ወግ የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል።”

[10] ሕዝቡንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙ፥ አስተውሉም።

[11] ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባው አይደለም፤ ከአፍ የሚወጣው ሰውን ያረክሰዋል እንጂ።”

[12] ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው “ፈሪሳውያን ንግግርህን ሰምተው እንደ አንጐራጐሩ ታውቃለህን?” አሉት።

[13] እርሱም መልሶ እንዲህ አለ ፥ “የሰማዩ አባቴ ያልተከላት ተክል ሁላ ትነቀላለች።

[14] እነርሱን ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸውና፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ወደ ጕuድጓድ ይወድቃሉ።”

[15] ጴጥሮስም መልሶ ፥ “ምሳሌዉን ተርጕuምልን ” አለው።

[16] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተም ገና ይህን አላስተዋላችሁምን?

[17] ወደ አፍ የሚገባው ሁሉ ወደ ሆድ እንደሚወርድ፥ ወደ ውጭም እንደሚወድቅ አታውቁምን?

[18] ከአፍ የሚወጣው ግን ከልብ ይወጣል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው።

[19] ከልብ ክፉ ዐሳብ ይወጣልና፤ ይኸውም መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ ስርቆት፥ በሐሰት መመስከር፥ ስድብም ነው።

[20] ሰውን የሚያረክሱት እነዚህ ናቸው፤ እጅን ሳይታጠቡ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም።”

[21] ጌታችን ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ።

[22] እነሆ፥ አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ ፥ “አቤቱ፥ የዳዊት ልጅ እዘንልኝ፤ ልጄን ክፉ ጋኔን ይዞ ያሠቃያታልና ” እያለች ጮኸች።

[23] ጌታችን ኢየሱስ ግን አንድም ቃል አልመለሰላትም፤ ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው ፥ “ይህችን ሴት አሰናብታት፤ እኛን እየተከተለች ትጮሃለችና ” ብለው ማለዱት።

[24] እርሱም መልሶ ፥ “ከእስራኤል ቤት ወደ ጠፉ በጎች ብቻ እንጂ አልተላክሁም ” አላቸው።

[25] እርስዋ ግን ቀርባ ፥ “አቤቱ፥ ርዳኝ ” ብላ ሰገደችለት።

[26] እርሱም መልሶ ፥ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መስጠት መልካም አይደለም ” አላት።

[27] እርስዋም ፥ “አዎን ጌታዬ ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ ” አለች።

[28] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ ፥ “አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደ ወደድሽ ይሁንልሽ ” አላት፤ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ ልጅዋ ዳነች።

[29] ጌታችን ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ ደረሰ፤ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ።

[30] ብዙ ሕዝብም ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ከእነርሱ ጋርም አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ደንቆሮዎችን፥ ልምሾዎችንና ሌሎችንም ብዙዎች በሽተኟችን አምጥተው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ እግር በታች አኖሩአቸው፤ እርሱም አዳናቸው።

[31] ሕዝቡም ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲድኑ፥ አንካሶች ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው፥ እስኪደነቁ ድረስ፥ የእስራኤልን አምላክ አመሰገኑት።

[32] ጌታችን ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ፥ “እነዚህ ሰዎች ያሳዝኑኛል፤ በዚህ ከእኔ ጋር ከዋሉ ሦስት ቀን ነውና፤ የሚበሉትም የላቸውም፤ በመንገድ እንዳይደክሙ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም ” አላቸው።

[33] ደቀ መዛሙርቱም ፥ “ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን?” አሉት።

[34] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም ፥ “ሰባት እንጀራ፥ ጥቂትም ዓሣ ” አሉት።

[35] ሕዝቡንም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤

[36] ሰባቱን እንጀራና ዓሣውን ይዞ አመሰገነ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ አቀረቡ።

[37] ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቐርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ።

[38] የበሉት ሰዎችም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ።

[39] ሕዝቡንም አሰናብቶ ወደ ታንኳው ገባ፤ ወደ መጌዶል አገርም ሄደ።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters