Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:47

[1] ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ከሰማይ ምልክትን ያሳያቸው ዘንድ ሊፈትኑት መጡ።

[2] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “በመሸ ጊዜ ሰማዩ ቀልትWaልና ጊዜው ብራ ነው ትላላችሁ።

[3] በነጋም ጊዜ ሰማዩ ደምኖ ቀልትWaልና ዛሬስ ይዘንማል ትላላችሁ፤ እናንተ ግብዞች፥ የሰማዩን ፊት መተርጐም ታውቃላችሁ፤ የዘመኑንስ ምልክት እንዴት አታውቁም?

[4] ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ትሻለች፤ ምልክት ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር አይሰጣትም ” ከዚህም በኋላ ትቶአቸው ሄደ።

[5] ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በደረሱ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረስተው ነበር።

[6] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ዕወቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ ” አላቸው።

[7] እነርሱም ፥ “እንጀራ አልያዝንምና እንዲህ ይለናል?” ብለው እርስ በርሳቸው ዐሰቡ።

[8] ጌታችን ኢየሱስም ዐውቆባቸው እንዲህ አላቸው ፥ “እናንት እምነት የጐደላችሁ፥ እርስ በርሳችሁ ምን ታስባላችሁ? እንጀራ ስለሌላችሁ ነውን?

[9] ገና አታስተውሉምን? በአምስቱ እንጀራ ጊዜስ ለአምስት ሺህ ሰዎች የሆነውን፥ ስንት መሶብም እንደ አነሣችሁ አታስቡምን?

[10] ወይስ ሰባት እንጀራ ለአራቱ ሺህ ሰው፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ እይላችሁምን?

[11] ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ ያልኋችሁ ስለ እንጀራ እንዳይደለ እንዴት አታስተውሉም?”

[12] ከዚህም በኋላ፥ ደቀ መዛሙርቱ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ፥ ከእንጀራ እርሾ ይጠበቁ ዘንድ እንዳልነገራቸው ያንጊዜ አስተዋሉ።

[13] ጌታችን ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ፥ “የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?” ብሎ ጠየቃቸው።

[14] እነርሱም ፥ “መጥምቁ ዮሐንስ ነው የሚሉ አሉ፤ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ፥ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ ” አሉት።

[15] እርሱም ፥ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው።

[16] ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ ፥ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ ” አለው።

[17] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው ፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ አንተ ብፁዕ ነህ፤ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና።

[18] እኔም እልሃለሁ፤ አንተ ዐለት ነህ፤ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፤ የሲኦል በሮችም አይበረታቱባትም።

[19] የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል።”

[20] ከዚህም በኋላ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይናገሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።

[21] ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች፥ ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዳለው ለደቀ መዛሙርቱ ይነግራቸው ጀመረ።

[22] ጴጥሮስም መልሶ ፥ “አቤቱ፥ ይህ አይሁንብህ፤ ከቶም አይድረስብህ ” እያለ ይከለክለው ጀመረ።

[23] ጌታችን ኢየሱስ ግን መለስ ብሎ ጴጥሮስን እንዲህ አለው ፥ “አንተ ሰይጣን! ከኋላዬ ሂድ፤ ዕንቅፋት ሆነህብኛል፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና።”

[24] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው ፥ “እኔን ሊከተል የሚወድ ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ።

[25] ነፍሱን ሊያድናት የሚወድ ይጥላታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚጥላት ያገኛታል።

[26] ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ፥ ነፍሱንም ቢያጣ፥ ለሰው ምን ይረባዋል? ሰውስ ለነፍሱ ቤዛ ምን በሰጠ ነበር?

[27] የሰው ልጅ መላእክቱን አስከትሎ በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፥ ያንጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ዋጋውን ይሰጠዋል።

[28] እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩት ድረስ፥ እዚህ ቆመው ካሉት ሞትን የማይቀምሱ አሉ።”

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters