Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:53

[1] “ለሰዎች ትታዩ ዘንድ፥ ምጿታችሁን በሰዎች ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው በአባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም።

[2] ምጿታችሁንም በምታደርጉበት ጊዜ፥ ግብዞች በሰዎች ዘንድ ሊመሰገኑ በምኵuራብና በአውራ ጎዳና እንደሚያደርጉት በፊታችሁ መለከት አታስነፉ፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።

[3] አንተስ ምጿትህን በምታደርግበት ጊዜ ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ።

[4] ምጿትህ በስውር ይሁን፤ በስውር የሚያይህ አባትህም በግልጥ ዋጋህን ይሰጥሃል።

[5] “በምትጸልዩበትም ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነርሱ ለሰው ይታዩ ዘንድ፥ በምኵuራብና በአደባባይ መዓዝን መቆምንና መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።

[6] አንተ ግን በምትጸልይበት ጊዜ ወደ ቤትህ ግባ፤ ደጅህንም ዘግተህ በስውር ወደ አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይህ አባትህም በግልጥ ዋጋህን ይሰጥሃል።

[7] ስትጸልዩም እንደ አሕዛብ ነገርን አታብዙ፤ እነርሱ ነገራቸውን በማብዛታቸው የሚሰማቸው ይመስላቸዋልና።

[8] አትምሰሏቸው፤ ሰማያዊው አባታችሁ ሳትለምኑት የምትሹትን ያውቃልና።

[9] እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በሉ ፥ ‘አባታችን ሆይ፥ በሰማያት የምትኖር ስምህ ይቀደስ።

[10] መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነ እንዲሁ በምድር ይሁን።

[11] የዕለት ምግባችንን ዛሬ ስጠን።

[12] በደላችንን ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል።

[13] አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን፤ ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ፤ መንግሥት የአንተ ናትና ኀይል፥ ምስጋና፥ ለዘለዓለሙ አሜን።’

[14] ለሰዎች በደላቸውን ይቅር ብትሉ፥ ሰማያዊው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር ይላችኋልና።

[15] ነገር ግን ለሰዎች በደላቸውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።

[16] “በምትጿሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ እንደ ጿሙ ለሰው ይታዩ ዘንድ መልካቸውን ይለውጣሉና፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።

[17] እናንተስ በምትጿሙበት ጊዜ ራሳችሁን ቅቡ፤ ፊታችሁንም ታጠቡ።

[18] በስውር ለሚያይ ለአባታችሁ እንጂ፥ ለሰዎች እንደ ጿማችሁ እንዳትታዩ፤ በስውር የሚያያችሁ አባታችሁም ዋጋችሁን በግልጥ ይሰጣችኋል።

[19] “ብልና ነቀዝ በሚያበላሹት፥ ሌቦችም ቈፍረው በሚሰርቁበት በምድር ለእናንተ መዝገብ አትሰብስቡ።

[20] ነገር ግን ብልና ነቀዝ በማያበላሹት፥ ሌቦችም ቈፍረው በማይሰርቁት በሰማይ ለእናንተ መዝገብን ሰብስቡ።

[21] መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ በዚያ ይኖራልና።

[22] “የሰውነትህ መብራቱ ዐይንህ ነው፤ ዐይንህ ብሩህ ቢሆን ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል።

[23] ዐይንህ ግን ታማሚ ቢሆን ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል፤ በአንተ ላይ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማህ እንዴት ይበዛ!

[24] ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አገልጋይ የለም፤ ያለዚያ አንዱን ይወዳል፤ ሁለተኛውንም ይጠላል፤ ወይም ለአንዱ ይታዘዛል፤ ለሁለተኛውም አይታዘዝም፤ እንግዲህ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።

[25] “ስለዚህም እላችኋለሁ፤ ለነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ለሥጋችሁም በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከምግብ አትበልጥምን? ሥጋስ ከልብስ አይበልጥምን?

[26] የማይዘሩና የማያጭዱ፥ በጎተራም የማይሰበስቡ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ ሰማያዊ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ ትበልጡ የለምን?

[27] ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?

[28] ስለ ልብስስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የምድረ በዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ እዩ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም።

[29] ነገር ግን እላችኋለሁ ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም።

[30] እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን፥ ነገም ወደ እሳት ምድጃ የሚጣለውን የምድረ በዳ ሣር እነሆ፥ እንደዚህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ ሃይማኖት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?

[31] እንግዲህ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ።

[32] ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይሹታልና፤ ለእናንተ ግን ሰማያዊ አባታችሁ ይህን ሁሉ እንድትሹ ያውቃል።

[33] እናንተስ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት፥ ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።

[34] ለነገ አትጨነቁ፤ ነገ ለራስዋ ታስባለችና፤ ለቀኒቱ ክፋቷ ይበቃታል።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters