Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:31

[1] ጌታችን ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዙን ከፈጸመ በኋላ፥ ሊሰብክና ሊያስተምር ወደ ከተሞቻቸው ሄደ።

[2] ዮሐንስም በእስር ቤት ሳለ፥ ክርስቶስ ያደረገውን ሰምቶ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ወደ እርሱ ልኮ፥

[3] “የሚመጣው አንተ ነህ? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ?” አለው።

[4] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሂዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት።

[5] ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶችም ይሄዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል።

[6] በእኔም የማይሰናከል ሁሉ ብፁዕ ነው።”

[7] እነዚያም ከሄዱ በኋላ፥ ጌታችን ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ ለሕዝቡ እንዲህ ይላቸው ጀመረ ፥ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጥታችኋል? ከነፋስ የተነሣ የሚወዛወዘውን ሸንበቆ ነውን?

[8] ወይስ ምን ልታዩ ወጥታችኋል? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን ነውን? እነሆ፥ ቀጭን ልብስ የሚለብሱስ በነገሥታት ቤቶች አሉ።

[9] ምን ልታዩ ወጥታችኋል? ነቢይን ነውን? አዎን፤ እሱ ከነቢይ እጅግ ይበልጣል እላችኋለሁ።

[10] እነሆ፤ እኔ በፊትህ መንገድህን የሚጠርግ መልእክተኛዬን በአንተ ፊት እልካለሁ ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈለት ይህ ነውና።

[11] እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን የሚያንሰው ይበልጠዋል።

[12] ከመጥምቁ ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ የተገፉትም ይናጠቁአታል።

[13] ነቢያትም ሁሉ፥ ኦሪትም እስከ ዮሐንስ ትንቢትን ተናግረዋልና።

[14] ልትቀበሉትስ ብትወድዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው።

[15] ዦሮ ያለው መስማትን ይስማ።

[16] “ይህቺን ትውልድ በምን እመስላታለሁ? በገበያ ተቀምጠው ጓደኟቻቸውን የሚጠሩ ልጆችን ትመስላለች።

[17] እንዲህም ይሏቸዋል ፥ እንቢልታ እየነፋን አቀነቀንላችሁ አልዘፈናችሁም፤ ሙሾም አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁም።

[18] ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ እነርሱ ግን ጋኔን አለበት አሉት።

[19] የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም እነሆ፥ የሚበላና የወይን ጠጅ የሚጠጣ፥ የቀራጮችና የኃጥኣን ወዳጅ ነው አሉት፤ ጥበብም ከልጆችዋ የተነሣ ጸደቀች።”

[20] ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ብዙ ተአምራት ያደረገባቸውን ከተሞች ንስሓ ስላልገቡ ይነቅፋቸው ጀመር፤ እንዲህም አላቸው።

[21] “ኮራዚ ወዮልሽ፤ ቤተ ሳይዳ ወዮልሽ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ማቅ ለብሰው፥ አመድም ነስንሰው አስቀድመው ንስሓ በገቡ ነበር።

[22] ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ጢሮስና ሲዶና ዕረፍትን ያገኛሉ።

[23] ቅፍርናሆም! አንቺም እስከ ሰማይ ከፍ ከፍ ብትዪ እስከ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺም የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን እስከ ዛሬ በኖረች ነበር።

[24] ነገር ግን እልሻለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ የሰዶም ምድር ዕረፍትን ታገኛለች።”

[25] ያንጊዜም ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ምሥጢር ከጥበበኟችና ከዐዋቆች ሰውረህ ለሕፃናት ገልጸኸዋልና አመሰግንሃለሁ።

[26] አዎን አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲሁ ሆኖአልና።

[27] ሁሉም ከአባቴ ዘንድ ተሰጠኝ፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቀው የለም፤ አብንም ከወልድ በቀር፥ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቀው የለም።

[28] እናንተ ደካሞች፥ ሸክማችሁም የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ።

[29] ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና፤ ልቤም ትሑት ነውና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍትን ታገኛላችሁ።

[30] ቀንበሬ ልዝብ፥ ሸክሜም ቀላል ነውና።”

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters