[1] ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀረቡ።
[2] አፉንም ከፈተ፤ እንዲህም ብሎ አስተማራቸው።
[3] “በመንፈስ ነዳያን የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
[4] ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና።
[5] የዋሃን ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ ምድርን ይወርሳሉና።
[6] ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ ይጠግባሉና።
[7] የሚራሩ ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ ምሕረትን ያገኛሉና።
[8] ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን ያዩታልና።
[9] ዕርቅን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።
[10] ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
[11] በሚሰድቧችሁና በሚያሳድዱአችሁ ጊዜ፥ ስለ እኔም እየዋሹ ክፉውን ሁሉ በሚናገሩባችሁ ጊዜ ብፁዓን ናችሁ።
[12] ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትንም አድርጉ፤ ዋጋችሁ በሰማያት ብዙ ነውና፤ ከእናንተ አስቀድሞ የነበሩ ነቢያትንም እንዲሁ አሳድደዋቸው ነበርና።
[13] “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን እንግዲህ በምን ይጣፍጣል? እንግዲህ የሚጠቅመው የለም፤ ሰዎች ወደ ውጭ አውጥተው ይጥሉታል፤ በእግራቸውም ይረግጡታል እንጂ።
[14] “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ መሰወር አይቻላትም።
[15] ከእንቅብ በታች ሊያኖሯት መብራትን አያበሩም፤ በመቅረዝዋ ላይ አኑረዋት በቤት ላሉት ሁሉ ታበራለች እንጂ።
[16] መልካሙን ሥራችሁን አይተው፥ በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።
[17] “ኦሪትንና ነቢያትን ልሽራቸው የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽማቸው ነው እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም።
[18] እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ አታልፍም።
[19] ከእነዚህ ከጥቃቅኑ ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር፥ ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግና የሚያስተምር ግን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል።
[20] አሁንም ጽድቃችሁ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማትገቡ እነግራችኋለሁ።
[21] “ለቀደሙት ሰዎች ‘አትግደል፥ የገደለም እርሱ ይፈረድበታል ’ የተባለውን ሰምታችኋል።
[22] እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ በከንቱ የሚቈጣ ሁሉ እርሱ ይፈረድበታል፤ ወንድሙንም ጨርቅ ለባሽ የሚለው በአደባባይ ይፈረድበታል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ በገሃነመ እሳት ይፈረድበታል።
[23] መባህን በመሠውያው በምታቀርብበት ጊዜ፥ በዚያም ሳለህ የተጣላህ ወንድምህ እንዳለ ብታስብ፥
[24] መባህን ከዚያ በመሠውያው ፊት ትተህ ሂድና አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚህ በኋላም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።
[25] በመንገድ ከእርሱ ጋር ሳለህ ከባለጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባለጋራህ ለዳኛ እንዳይሰጥህ፤ ዳኛውም አሳልፎ ለሎሌው ይሰጥሀል፤ ወደ እስር ቤትም ትገባለህ።
[26] እውነት እልሀለሁ፤ የመጨረሻውን ትንሽ ገንዘብ እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።
[27] ለቀደሙት ሰዎች ‘አታመንዝር ’ የተባለውን ሰምታችኋል።
[28] እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን አይቶ የተመኛት ሁሉ ፈጽሞ በልቡ አመነዘረባት።
[29] ቀኝ ዐይንህ ብታስትህ፥ ከአንተ አውጥተህ ጣላት፤ ሁለት ዐይና ሆነህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትገባ ይልቅ፥ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና።
[30] ቀኝ እጅህም ብታስትህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ አካልህ ሁሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካልህ አንዱ ቢጠፋ ይሻላልና። ቀኝ እግርህም ብታስትህ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ አካልህ ሁሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካልህ አንዱ ቢጠፋ ይሻላልና።
[31] “ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ፤ የፍችዋን ደብዳቤ ይስጣት ተብሏል።
[32] እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እርሱ ራሱ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።
[33] “ዳግመኛም ለቀደሙት ሰዎች፥ መሐላችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ እንጂ በሐሰት አትማሉ የተባለውን ሰምታችኋል።
[34] እኔ ግን እላችኋለሁ ፥ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና።
[35] በምድርም ቢሆን፥ የእግሩ መረገጫው ናትና፤ በኢየሩሳሌምም ቢሆን፥ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና።
[36] በራሳችሁም ቢሆን አትማሉ፤ ከራስ ጠጕuራችሁ አንዲቱን ነጭ ማድረግ ወይም ጥቐር ማድረግ አትችሉምና።
[37] ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን፥ ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከእነዚህም የወጣ ከክፉ ወገን ነው።
[38] “ለቀደሙት ሰዎች ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስም ስለ ጥርስ የተባለውን ሰምታችኋል።
[39] እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ክፉን በክፉ አትቃወሙት፤ ቀኝ ፊትህን ለሚመታህ ግራ ፊትህን መልስለት።
[40] ቀሚስህንም ሊቀማህ ለሚሻ መጐናጸፊያህን ተውለት።
[41] አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለት ምዕራፍ አብረኸው ሂድ።
[42] ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ከአንተም ሊበደር የሚወደውን አትከልክለው።
[43] “ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህንም ጥላ የተባለውን ሰምታችኋል።
[44] እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድሉአችሁና ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ።
[45] በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ፤ እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐይን ያወጣልና፥ ለጻድቃንና ለኃጥኣንም ዝናምን ያዘንማልና።
[46] የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ ዋጋችሁ ምንድን ነው? እንደዚህማ ቀራጮችስ ያደርጉ የለምን?
[47] ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ ብትነሡ፥ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን?
[48] እንግዲህ ሰማያዊው አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።”