Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:36

[1] ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ያወጡአቸው ዘንድ፥ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ ይፈውሱ ዘንድ በርኩሳን መናፍስት ላይ ሥልጣንን ሰጣቸው።

[2] የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያትም ስማቸው እንዲህ ነው፤ መጀመሪያው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን፥ ወንድሙ እንድርያስም፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብም፥ ወንድሙም ዮሐንስ፤

[3] ፊልጶስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ቶማስም፥ ቀራጩ ማቴዎስም፥ የዕልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ታዴዎስ የተባለ ልብድዮስም፤

[4] ቀነናዊው ስምዖን፥ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ሰው ይሁዳም።

[5] ጌታችን ኢየሱስ እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ላካቸው፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፤ “በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያን ከተማም አትግቡ።

[6] ነገር ግን ከእስራኤል ወገን ወደ ጠፉ በጎች ሂዱ።

[7] ሄዳችሁም መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች እያላችሁ አስተምሩ።

[8] ድውያንን ፈውሱ፤ ሙታንንም አንሡ፤ ለምጻሞችንም አንጹ፤ አጋንንትንም አውጡ፤ ያለ ዋጋ የተቀበላችሁትን ያለ ዋጋ ስጡ።

[9] በመቀነታችሁም ወርቅ፥ ወይም ብር፥ ወይም መሐለቅ አትያዙ።

[10] ለመንገድም ስልቻ፤ ወይም ሁለት ልብስ፥ ወይም ጫማ፥ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋልና።

[11] በምትገቡባትም በማንኛዪቱም ከተማ፥ ወይም መንደር በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ።

[12] ወደ ቤትም በገባችሁ ጊዜ፥ ሰላምታ ስጡአቸው።

[13] ለዚያ ቤት የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይደርበት፤ የማይገባው ቢሆን ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ።

[14] ከማይቀበላችሁ፥ ቃላችሁንም ከማይሰማችሁ ግን ከዚያች ቤት፥ ወይም ከዚያች ከተማ ወጥታችሁ፥ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።

[15] ከዚያች ሀገር ይልቅ በፍርድ ቀን ሰዶምና ገሞራ ዕረፍት እንደሚያገኙ በእውነት እነግራችኋለሁ።

[16] “እነሆ እኔ እንደ በጎች በተኵuላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ እንግዲህ እንደ እባብ ብልሆች፥ እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።

[17] ከክፉዎች ሰዎች ተጠበቁ፤ ወደ አደባባዮችም አሳልፈው ይሰጡአችኋልና፤ በምኵuራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና።

[18] ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር ትሆኑ ዘንድ ስለ እኔ ወደ መሳፍንትና ወደ ነገሥታት ይወስዱአችኋል።

[19] አሳልፈው በሰጧችሁ ጊዜ፥ እንዴት ወይም ምን እንደምትናገሩ አትጨነቁ፤ በዚያች ሰዓት የምትናገሩት ይሰጣችኋልና።

[20] የሰማያዊው አባታችሁ መንፈስ እርሱ በእናንተ ላይ አድሮ ይናገራል እንጂ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።

[21] ወንድምም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ፤ ይገድሉአቸዋልም።

[22] ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ ፍጻሜ የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል።

[23] ከዚያች ከተማ ቢአሳድዱአችሁ ወደ ሌላዪቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ፥ የእስራኤል ከተሞች አይፈጸሙም።

[24] ከመምህሩ የሚበልጥ ደቀ መዝሙር፥ ከጌታውም የሚበልጥ አገልጋይ የለም።

[25] ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፥ አገልጋይም እንደ ጌታው ከሆነ ይበቃዋል። ባለቤቱን በሰይጣናት አለቃ ሰይጣናትን ያወጣል ካሉት፥ ቤተ ሰቡንማ እንደ ምን ከዚህ አብልጠው አይናገሩአቸው?

[26] “እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ የለምና፤ የማይታወቅም የተሰወረ የለምና።

[27] በጨለማ የነገርሁአችሁን በብርሃን ተናገሩት፤ በጆሮአችሁ በሹክሹክታ የነገርሁዋችሁንም በሰገነት ላይ ስበኩት።

[28] ሥጋችሁንም የሚገድሉትን አትፍሩአቸው፤ ነፍሳችሁን ግን ሊገድሉአት አይችሉም፤ ነገር ግን ነፍስንም ሥጋንም አንድ አድርጎ በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን እርሱን ፍሩት።

[29] ሁለት ወፎች በሁለት መሐለቅ ይሸጡ የለም? ከእነርሱ አንዲትWa እንኳ ሰማያዊው አባታችሁ ሳያውቅ በምድር ላይ አትወድቅም።

[30] የእናንተስ የራስ ጠጕuራችሁ ሁሉ እንኳን የተቈጠረ ነው።

[31] እንኪያስ አትፍሩ፤ ከብዙ ወፎች እናንት ትበልጣላችሁና።

[32] በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ፤ እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ።

[33] በሰው ፊት የሚክደኝን ግን፥ እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ።

[34] “በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።

[35] ወንድ ልጅን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናቷ፥ ምራትንም ከአማቷ ልለይ መጥቻለሁ።

[36] ለሰውም ጠላቶቹ ቤተ ሰቦቹ ይሆኑበታል።

[37] ከእኔ ይልቅ አባቱንና እናቱን የሚወድድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔም ይልቅ ወንድ ልጁንና ሴት ልጁን የሚወድድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።

[38] መስቀሉንም ተሸክሞ እኔን በኋላዬ የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።

[39] ነፍሱን የሚያገኛት ያጠፋታል፤ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋት ያገኛታል።

[40] “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።

[41] በነቢይም ስም ነቢይን የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይቀበላል፤ በጻድቅም ስም ጻድቅን የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ይቀበላል።

[42] ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ በደቀ መዝሙሬ ስም ቀዝቃዛ ጿ ውኃ ብቻ የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋውን አያጣም።”

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters