Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:07

[1] ከወንድሞቻችሁ ጋር በፍቅር ኑሩ።

[2] እንግዳ መቀበልንም አትርሱ፤ በዚህ ምክንያት ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ለመቀበል ያታደሉ አሉና።

[3] ከእነርሱ ጋር አብራችኋቸው እንደ ታሰራችሁ ሆናችሁ እስረኟችን ዐስቡ፤ መከራ የጸናባቸውንም በሥጋችሁ ከእነሱ ጋር እንዳላችሁ ሆናችሁ ዐስቡ።

[4] መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፥ ለመኝታቸውም ርኵuሰት የለውም፤ ሴሰኟችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።

[5] ገንዘብ ሳትወዱ ኑሩ፤ ያላችሁም ይበቃችኋል፤ እርሱ “አልጥልህም፤ ቸልም አልልህም ” ብሎአልና።

[6] አሁንም አምነን ፥ “እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ አልፈራም፥ ሰው ምን ያደርገኛል?” እንበል።

[7] የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው።

[8] ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለም የሚኖር እርሱ ነውና።

[9] ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና።

[10] ድንኳኒቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ከእርሱ ሊበሉ የማይቻላቸው መሠዊያ አለን፤

[11] ሊቀ ካህናቱ የሚሠዉትን እንስሳ ደም ስለ ኀጢአት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያቀርብ ነበርና፤ ሥጋውንም ከሰፈር ውጭ ያቃጥሉት ነበር።

[12] ስለዚህም ኢየሱስ ሕዝቡን በደሙ ይቀድሳቸው ዘንድ ከከተማ ውጭ ተሰቀለ።

[13] አሁንም ተግዳሮቱን ተሸክመን፥ ወደ እርሱ ወደ ከተማው ውጭ እንውጣ።

[14] በዚህ የሚኖር ከተማ ያለን አይደለም፤ የምትመጣውን እንሻለን እንጂ።

[15] በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን?

[16] ነገር ግን ለድሆች መራራትን፥ ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።

[17] ለመምህሮቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ ስለ እናንተ በእግዚአብሔር ፊት ምላሽ የሚሰጡ እንደ መሆናቸው፥ ይህን ሳያዝኑ ደስ ብሎአቸው ያደርጉት ዘንድ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና።

[18] ይህም ስለ እኛ ትጸልዩ ዘንድ ይገባችኋል፤ ለሁሉ መልካም ነገርን እንደምትወዱና እንደምትሹ እናምናለን።

[19] ይልቁንም ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ።

[20] በዘለዓለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው፥

[21] የሰላም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።

[22] ወንድሞች ሆይ፥ የምክርን ቃል እንድትቀበሉ እመክራችኋለሁ፤ በጥቂት ቃል ጽፌላችኋለሁና።

[23] ወንድማችን ጢሞቴዎስ ከእኛ ወደ እናንተ እንደ ተላከ ዕወቁ፤ ፈጥኖ ከመጣ አያችኋለሁ።

[24] መምህሮቻችሁን ሁሉና ቅዱሳንንም ሁሉ ሰላም በሉ፥ በኢጣልያ ያሉ ሁሉ ሰላም ብለዋችኋል።

[25] የጌታችን ጸጋዉ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። ወደ ዕብራውያን የተላከው መልእክት ተፈጸመ፤ በኢጣልያ ተጻፈ፤ በጢሞቴዎስ እጅ ተላከ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።

ወደ ዕብራውያን — Chapters