Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:12

[1] ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና።

[2] እርሱ ራሱም ደካማ ነውና ባለማወቃቸው ከሳቱ ሰዎች ጋር መከራን ሊቀበል ይችላል።

[3] በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኀጢአት ማቅረብ ይገባዋል።

[4] እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር፥ ማንም ለራሱ ክብርን የሚወስድ የለም።

[5] እንዲሁ ክርስቶስም ሊቀ ካህናት ይሆን ዘንድ ራሱን ያከበረ አይደለም፤ ነገር ግን ፥ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔም ዛሬ ወለድሁህ ” ያለው እርሱ ራሱ ነው።

[6] ዳግመኛም ፥ “እንደ መልከ ጽዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን አንተ ነህ ” ይላል።

[7] እርሱም ሥጋ ለብሶ በዚህ ዓለም በነበረበት ጊዜ፥ በታላቅ ጩኸትና እንባ ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ ጽድቁንም ሰማው።

[8] ልጅም ቢሆን መከራን ስለ ተቀበለ መታዘዝን ዐወቀ።

[9] ከተፈጸመም በኋላ ለሚታዘዝለት ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ የዘለዓለም መድኅን ሆነ።

[10] እግዚአብሔርም እንደ መልከ ጽዴቅ ሹመት የዘለዓለም ሊቀ ካህናት አለው።

[11] ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ጆሮዎቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕuመው ጭንቅ ነው።

[12] መምህራን ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ ካመናችሁ ጀምሮ በትምህርት ላይ የቈያችሁ ስለ ሆነ፥ እስከ ዛሬም ገና የእግዚአብሔርን የቃሉን መጀመሪያ ትምህርት ሊያስተምሩአችሁ ትወዳላችሁ፤ ወተትንም ሊግቱአችሁ ትሻላችሁ፤ ጽኑ ምግብንም አይደለም።

[13] ወተትን የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ፥ የጽድቅን ቃል ሊያውቅ አይሻም።

[14] ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉዉን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።

ወደ ዕብራውያን — Chapters