[1] እምነትስ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ፥ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት።
[2] በዚህም ለሽማግሌዎች ተመሰከረላቸው።
[3] ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠረ፥ የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንደ ሆነ በእምነት እናውቃለን።
[4] አቤል ከቃኤል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ምስክሩም መሥዋዕቱን በመቀበል እግዚአብሔር ነው። በዚህም ከሞተ በኋላ እንኳ ተናገረ።
[5] ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም፤ ሳይወሰድም እግዚአብሔርን ደስ እንደ አሰኘው ተመስክሮለታል።
[6] ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው አስቀድሞ እግዚአብሔር እንዳለ፥ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጣቸው ሊያምን ይገባዋል።
[7] ኖኅም ስለማይታየው ነገር የነገሩትን ባመነ ጊዜ ፈራ፤ ቤተ ሰቡንም ያድን ዘንድ ክፍል ያላት መርከብን ሠራ፤ በዚህም ዓለምን አስፈረደበት፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።
[8] አብርሃም በተጠራ ጊዜ ርስት አድርጎ ይወርሰው ዘንድ ወዳለው ሀገር ለመሄድ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚደርስም ሳያውቅ ሄደ።
[9] በእምነትም ከሀገሩ ወጥቶ ተስፋ በሰጠው ሀገር እንደ ስደተኛ በድንኳን፥ ተስፋውን ከሚወርሱአት ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ኖረ።
[10] መሠረት ያላትን ሠሪዋና ፈጣሪዋ እግዚአብሔር የሆነላትን ከተማ ደጅ ይጠኑ ነበርና።
[11] ራስዋ ሳራም መካን ሳለች ባረጀችበት ወራት ዘር ታስገኝ ዘንድ በእምነት ኀይልን አገኘች፤ ተስፋ የሰጣት የታመነ እንደ ሆነ አምናለችና።
[12] ስለዚህም ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ፥ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ።
[13] እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፤ ተስፋቸውንም አላገኙም፤ ነገር ግን ከሩቅ አይተው እጅ ነሱኣት፤ በምድሪቱም ላይ እነርሱ እንግዶችና መጻተኟች እንደ ሆኑ ዐወቁ።
[14] እንዲህ የሚሉ ግን ሀገራቸውን እንደሚሹ ያሳያሉ።
[15] ከእርስዋ የወጡባትን ሀገር ቢሹ ኖሮስ፥ ወደ እርስዋ ሊመለሱ በተቻላቸው ነበር።
[16] አሁን ግን፥ በሰማያት ያለችውን የምትበልጠውን ሀገር ተስፋ ያደርጉ እንደ ነበር ታወቀ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ይጠራ ዘንድ በእነርሱ አያፍርም፤ ተስፋ ያደረጉአትን ሀገር አዘጋጅቶላቸዋልና።
[17] አብርሃምም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ ልጁን ይስሐቅን ይሠዋው ዘንድ በእምነት ወሰደው።
[18] “በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ” ብሎ ተስፋ ያናገረለትን አንድ ልጁን አቀረበው።
[19] እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ ሊያስነሣው እንደሚችል አምኖአልና፤ ስለዚህም ያው የተሰጠው መታሰቢያ ሆነለት።
[20] ያገኙት ዘንድ ስለ አላቸው ነገር ይስሐቅ ያዕቆብንና ኤሳውን በእምነት ባረካቸው።
[21] ያዕቆብም በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን በእምነት ባረካቸው፤ በበትሩ ጫፍም ሰገደ።
[22] ዮሴፍም በሚሞትበት ጊዜ፥ ስለ እስራኤል ልጆች ከግብፅ መውጣት በእምነት ዐሰበ፤ ዐጽሙንም ትተው እንዳይወጡ አዘዘ።
[23] ሙሴ በተወለደ ጊዜ በእምነት ሦስት ወር በአባቱ ቤት ሸሸጉት፤ ሕፃኑ መልካም እንደ ሆነ አይተውታልና፤ የንጉሥንም ትእዛዝ አልፈሩም።
[24] ሙሴም በአደገ ጊዜ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እንቢ አለ፤
[25] ለጊዜው በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ።
[26] የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት ከግብፅ ሀብት ሁሉ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንደሚሆን ዐውቆአልና፥ ዋጋውንም ተመልክቶአልና።
[27] የንጉሡንም ቐጣ ሳይፈራ፥ የግብፅን ሀገር በእምነት ተወ፤ ከሚያየው ይልቅ የማይታየውን ሊፈራ ወዶአልና።
[28] ቸነፈር በኵuራቸውን እንዳያጠፋባቸው በእምነት ፋሲካን አደረገ፤ ደሙንም ረጨ።
[29] በደረቅ ምድር እንደ መሄድ የኤርትራን ባሕር በእምነት ተሻገሩአት፤ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ሰጠሙ።
[30] ሰባት ቀን ከዞሩአት በኋላ የኢያሪኮ ቅጽር በእምነት ወደቀ።
[31] ዘማ ረአብም በእምነት ከከሓዲዎች ጋር አልጠፋችም፤ ጕuበኟችን በሰላም ተቀብላ ሰውራቸዋለችና።
[32] እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎን፥ ስለ ባርቅ፥ ስለ ሶምሶን፥ ስለ ዮፍታሔ፥ ስለ ዳዊት፥ ስለ ሳሙኤልና ስለ ሌሎች ነቢያት እነግራችሁ ዘንድ ጊዜዬ አጭር ነውና። 1፥1፥1ነገ. 2፥11።
[33] እነርሱ በእምነት ተጋደሉ፤ ነገሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ ተስፋቸውን አገኙ፤ የአናብስትንም አፍ ዘጉ ።
[34] የእሳት ኀይልን አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፤ በጦርነት ኀይለኟች ሆኑ፤ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩ።
[35] ሴቶችም እንደ ትንሣኤ ቀን ተነሥተውላቸው ሙታኖቻቸውን ተቀበሉ፤ ተፈርዶባቸው የሞቱም አሉ፤ የምትበልጠውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ ሊድኑ አልወደዱምና።
[36] የገረፉአቸው፥ የዘበቱባቸውና ያሠሩአቸው ወደ ወህኒ ያገቡአቸውም አሉ።
[37] በመጋዝ የሰነጠቁአቸው፥ በድንጋይ የወገሩአቸው፥ በሰይፍም ስለት የገደሉዋቸው አሉ፤ ማቅ፥ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፤ ተቸገሩ፤ መከራ ተቀበሉ፤ ተራቡ፥ ተጠሙም።
[38] ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፥ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ።
[39] እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙም።
[40] ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ፥ እግዚአብሔር ስለ እኛ የምትበልጠውን አስቀድሞ በይኖአልና።