Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:37

[1] አሁንም ከሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞቻችን ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ።

[2] ሙሴ ደግሞ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደ ሆነ፥ እርሱ ለላከው የታመነ እውነተኛ ነው።

[3] ነገር ግን የባለቤት ክብሩ ከቤቱ እንደሚበልጥ፥ ክብሩ ከሙሴ ክብር ይልቅ እጅግ ይበልጣል፤

[4] ቤትን ሁሉ ሰው ይሠራዋልና፤ ለሁሉ ግን ሠሪው እግዚአብሔር ነው።

[5] ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምስክር ሊሆን በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ ነበረ።

[6] ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ የታመነ ነው፤ እኛም የምንደፍርበትን፥ የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን።

[7] መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ብሎአልና ፥ “ዛሬ ቃሉን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ።

[8] በምድረ በዳ በተፈታተኑበት ቀን እንደ አሳዘኑት ጊዜ።

[9] የተፈታተኑኝ አባቶቻችሁ ፈተኑኝ፤ አርባ ዘመንም ሥራዬን አዩ።

[10] ስለዚህ ይህቺን ትውልድ ተቈጣኋት፤ እንዲህም አልሁ ፥ ‘ልባቸው ዘወትር ይስታል፤ እነርሱ ግን መንገዴን አላወቁም።’

[11] ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቐጣዬ ማልሁ።”

[12] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እንግዲህ ዕወቁ፤ ከእናንተ ባንዱ ላይ ስንኳ ሃይማኖት የጐደለውና ተጠራጣሪ፥ ከሕያው እግዚአብሔር የሚለያችሁ ክፉ ልብ አይኑር።

[13] ዛሬ የሚባለው ቀን ሳለ ከእናንተ ማንም ቢሆን ወደ ኀጢአት በሚያደርስ ስሕተት እንዳይጸና ሁልጊዜ ሰውነታችሁን መርምሩ።

[14] በዚች ጽድቅ እስከ መጨረሻ የቀደመውን ሥርዐታችንን አጽንተን ከጠበቅን ከክርስቶስ ጋር አንድ ሁነናልና።

[15] “ዛሬ ቃሉን ብትሰሙ እነዚያ እንደ አሳዘኑት ጊዜ ልባችሁን አታጽኑ ” ብሎአልና።

[16] ሰምተው ያሳዘኑትስ እነማን ናቸው? በሙሴ እጅ ከግብፅ የወጡት ሁሉ አይደሉምን?

[17] አርባ ዘመን የተቈጣቸውስ እነማን ነበሩ? የበደሉ፥ ሬሳቸውም በምድረ በዳ የወደቀው አይደሉምን?

[18] ከካዱት በቀር ወደ ዕረፍቱ እንዳይገቡ በማን ላይ ማለ?

[19] አላመኑምና፥ ለመግባት እንዳልቻሉ እነሆ፥ እናያለን።

ወደ ዕብራውያን — Chapters