Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:29

[1] ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፤ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም።

[2] ይህስ ባይሆን ከሚሠዉት መሥዋዕት ባረፉ ነበር፥ ለሚሠዉት ኀጢአታቸውን ያስተሰርይላቸው ነበርና፥ ባአንድ ጊዜም ያነጻቸው ነበርና።

[3] ነገር ግን በዚያው መሥዋዕት በየዓመቱ የኀጢአት መታሰቢያ አድርገው የሚያቀርቡት ነበራቸው።

[4] የላምና የፍየል ደም ኀጢአትን ሊያስተሰርይ አይችልምና።

[5] ስለዚህም ወደ ዓለም በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ አለ፥ “መሥዋዕትንና ቐርባንን አልወደድህም፤ ሥጋን አለበስኸኝ እንጂ።

[6] በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኀጢአት በሚቀርበው መሥዋዕት ደስ አላለህም።

[7] ያንጊዜ እነሆ፥ በመጽሐፍ ራስ ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን አደርግ ዘንድ መጥቻለሁ አልሁ።”

[8] በዚህ ላይ “መሥዋዕትንና መባን፥ በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም፥ ስለ ኀጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፤ በእርሱም ደስ አላለህም ” ብሎ ተናገረ፤ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡ ናቸው።

[9] ከዚህ በኋላ፥ “አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን አደርግ ዘንድ እነሆ፥ መጣሁ ” አለ፤ ይህ ቃል የኋለኛውን ያቆም ዘንድ የፊተኛውን ያፈርሳል።

[10] በፈቃዱም አንድ ጊዜ በተደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋዉ ቐርባን ተቀደስን።

[11] ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዘወትር እያገለገለ ይቆም ነበር፤ ፈጽሞ ኀጢአት ማስተስረይ የማይቻላቸውን እነዚያን መሥዋዕቶች ብቻም ይሠዋ ነበር።

[12] እርሱ ግን ስለ ኀጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘለዓለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ።

[13] እንግዲህ ጠላቶቹ ከእግሩ በታች እስኪወድቁ ድረስ ይጠብቃል።

[14] ለሚቀደሱትም ለዘለዓለም የምትሆን አንዲት መሥዋዕትን ሠዋ።

[15] መንፈስ ቅዱስም ምስክራችን ነው።

[16] “ከእነዚያ ወራቶች በኋላ የምገባላቸው ኪዳን ይህቺ ናት ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልባቸው አኖረዋለሁ፤ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ ካለ በኋላ።

[17] ከእንግዲህ ወዲህ ኀጢአታቸውንና በደላቸውን ደግሜ አላስብባቸውም ” ብሏል።

[18] እንዲህም ኀጢአት የሚሰረይ ከሆነ፥ እንግዲህ ወዲህ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት አያስፈልግም።

[19] እንግዲህ ወንድሞቻችን ሆይ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ወደ መቅደስ ለመግባት ባለሙአልነት አለን።

[20] በሥጋው መጋረጃ በኩል የሕይወትንና የጽድቅን መንገድ ፈጽሞ አድሶልናልና።

[21] በእግዚአብሔር ቤት ታላቅ ካህን አለን።

[22] እንግዲህ ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፥ ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ።

[23] እንግዲህ የማይናወጠውን የተስፋችንን እምነት እናጽና፤ ተስፋ የሰጠ እርሱ የታመነ ነውና።

[24] በፍቅርና በበጎ ምግባርም ከባልንጀሮቻችን ጋር እንፎካከር።

[25] ሌሎች ልማድ አድርገው እንደ ያዙት ማኅበራችንን አንተው፤ እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።

[26] እውነትን ካወቅናት በኋላ፥ ተጋፍተን ብንበድል ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት አይኖርም።

[27] ነገር ግን የሚያስፈራ ፍርድ ከሓዲዎችንም የሚበላቸው የቅናት እሳት ይጠብቃቸዋል።

[28] ከሙሴ ሕግ የተላለፈ ቢኖር ሁለት፥ ወይም ሦስት ምስክሮች ከመሰከሩበት ያለ ምሕረት ይሞታል።

[29] የእግዚአብሔርን ልጅ የከዳ፥ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቈጠረ፥ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?

[30] “እኔ እበቀላለሁ፤ እኔም ብድራትን እመልሳለሁ፥” ያለውን እናውቀዋለንና፤ ዳግመኛም “እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል።”

[31] በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው።

[32] እናንተ የተጠመቃችሁበትንና ብዙ መከራ የታገሣችሁበትን የቀደመውን ዘመን አስቡ፤

[33] እናንተ ተሰድባችሁ ነበር፤ መከራም አጽንተውባችሁ ነበር፤ ተዘባብተውባችሁም ነበር፤ በዚህም መንገድ እንዲህ ከሆኑት ጋር ተባብራችሁ ነበር።

[34] በእስራቴም ጊዜ ከእኔ ጋር በመከራ ተባብራችኋል፤ የገንዘባችሁንም መዘረፍ በደስታ ተቀብላችኋል፤ በሰማያት ለዘለዓለም የሚኖር ከዚህ የሚበልጥና የተሻለ ገንዘብ እንዳላችሁ ታውቃላችሁና።

[35] ትልቁን ዋጋችሁን የምታገኙባትን መታመናችሁን አትጣሉ።

[36] ነገር ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን ተስፋ ታገኙ ዘንድ መታገሥ ያስፈልጋችኋል።

[37] “ገና ጥቂት ቀን አለና፤ የሚመጣውም ፈጥኖ ይደርሳል፥ አይዘገይምም።

[38] ጻድቅ በእምነት ይድናል፤ ወደኋላ ቢመለስ ግን ልቡናዬ በእርሱ ደስ አይላትም።”

[39] እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑት ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉት አይደለንም።

ወደ ዕብራውያን — Chapters