Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:08

[1] ስለዚህም ከሰማነው ነገር ምንአልባት እንዳንወሰድ ለእርሱ አብዝተን ልንጠነቀቅ ይገባናል።

[2] በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥

[3] እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበረና የሰሙትም ለእኛ አጸኑት።

[4] እግዚአብሔርም እንደ ራሱ ፈቃድ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በመስጠት፥ በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በልዩ ልዩ ተአምራትም መሰከረላቸው፤ ነገራቸውንም አስረዳላቸው።

[5] ስለ እርሱ የምንናገርለትን የሚመጣውን ዓለም ለመላእክት ያስገዛ አይደለም።

[6] ነገር ግን መጽሐፍ እንዲህ ብሎ የመሰከረበት ስፍራ አለ፤ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጐበኘውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?

[7] ከመላእክትህ ጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድንም ጫንህለት፤ በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው።

[8] ሁሉንም ከእግሩ በታች አድርገህ አስገዛህለት።” ሁሉን ለእርሱ ባስገዛለት ጊዜም የተወውና ያላስገዛለት የለም፤ አሁን ግን ሁሉን እንዳስገዛለት አናይም።

[9] ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ጭኖ እናየዋለን።

[10] ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእጁ ለተያዘ፥ በእርሱም ሁሉ ለሆነ ለእርሱ ተገብቶታልና።

[11] እነርሱን የቀደሳቸው እርሱ፥ የተቀደሱት እነርሱም ሁሉም በአንድነት ከአንዱ ናቸውና። ስለዚህም እነርሱን ፥ “ወንድሞቼ ” ማለትን አያፍርም።

[12] “ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፤ በማኅበር መካከልም አመሰግንሃለሁ ” አለ።

[13] ዳግመኛም ፥ “እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች እነሆ፥” አለ፤ ዳግመኛም ፥ “እኔ እታመንበታለሁ ” አለ።

[14] ልጆች በሥጋና በደም አንድ ናቸውና፤ እርሱ ደግሞ በዚህ ከእነርሱ ጋር አንድ ሆነ፤ ለእነርሱም እንደ ወንድም ሆነላቸው፤ መልአከ ሞትን በሞቱ ይሽረው ዘንድ፥ ይኸውም ሰይጣን ነው።

[15] በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሞትን በመፍራት የተቀጡትን፥ ለባርነት የተገዙትንም ሁሉ ያሳርፋቸው ዘንድ።

[16] የነሣውን ከአብርሃም ዘር እንጂ ከመላእክት የነሣው አይደለምና።

[17] ስለዚህም የሕዝብን ኀጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።

[18] እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።

ወደ ዕብራውያን — Chapters