Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:57

[1] ፊተኛይቱም ደግሞ የአገልግሎት ሥርዐትና የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ ነበራት።

[2] የመጀመሪያዪቱም ድንኳን ተዘጋጅታ ነበርና፥ በእርስዋም ቅድስት በምትባለው ውስጥ መቅረዙና ጠረጴዛው፥ የመሥዋዕቱም ኅብስት ነበረባት።

[3] ከሁለተኛው መጋረጃ በስተኋላ የነበረችውን የውስጠኛዪቱን ድንኳን ግን ቅድስተ ቅዱሳን ይሉአት ነበር።

[4] በውስጥዋም የወርቅ ማዕጠንትና ሁለንተናዋን በወርቅ የለበጡአት፥ የኪዳን ታቦት፥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የለመለመችው የአሮን በትር፥ የኪዳኑም ጽላት ነበሩባት።

[5] በላይዋም ማስተስረያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ ነገር ግን በየመልኩ እናገረው ዘንድ ዛሬ ጊዜው አይደለም።

[6] ሥርዐቱ፥ ዝግጅቱም እንዲህ ነበር፤ በመጀመሪያዪቱም ድንኳን በየጊዜው አገልግሎታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ፥ ካህናት ዘወትር ይገቡ ነበር።

[7] ወደ ሁለተኛዪቱ ክፍል ግን ሊቀ ካህናቱ ኀጢአታቸውን ለማስተስረይ ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ የሚያቀርበውን ደም ይዞ፥ በየዓመቱ አንድ ጊዜ ብቻውን ይገባ ነበር።

[8] ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል።

[9] ነገር ግን ለሚያቀርበው ሰው ግዳጅ መፈጸም የማይቻለውን መባና መሥዋዕት ያቀርቡበት የነበረው ለዚህ ዘመን ምሳሌ ሆነ።

[10] እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም፥ ስለ ልዩ ልዩ ጥምቀትም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዐቶች ብቻ ናቸው።

[11] ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ የሰው እጅ ወደ አልሠራት፥ በዚህ ዓለም ወደ አልሆነችው፥ ከፊተኛዪቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን፥

[12] የዘለዓለም መድኀኒትን ገንዘብ አድርጎ፥ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም።

[13] የላምና የፍየል ደም፥ በረከሱትም ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ፥ የሚያነጻና የረከሱትንም ሥጋቸውን የሚቀድሳቸው ከሆነ፥

[14] ነውር የሌለው ሆኖ፥ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እናመልከው ዘንድ ሕሊናችንን ከሞት ሥራ እንዴት ይልቅ ያነጻ ይሆን?

[15] ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ተቀብሎ፥ በቀደመው ሥርዐት ስተው የነበሩትን ያድናቸው ዘንድ ወደ ዘለዓለም ርስቱም የጠራቸው ተስፋውን ያገኙ ዘንድ፥ ለአዲሲቱ ኪዳን መካከለኛ ሆነ።

[16] ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡ ሰው ሞት ይመጣ ዘንድ ግድ ነው።

[17] የሙአች ሰው ኑዛዜ የጸናች ናት፤ ተናዛዡ በሕይወት ባለበት ጊዜ አትጠቅምምና።

[18] ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አልከበረም።

[19] ሙሴ የኦሪትን ትእዛዝ ሁሉ ለመላው ሕዝብ ከነገረ በኋላ፥ የላምና የፍየል ደም ከውኃ ጋር ቀላቅሎ፥ ቀይ የበግ ጠጕuርና የስሚዛ ቅጠል ነክሮ መጽሐፈ ኦሪቱንና ሕዝቡን ሁሉ ይረጭ ነበር።

[20] “እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው ” ይላቸው ነበር።

[21] ድንኳኑንና የመገልገያውን ዕቃ ሁሉ በደሙ ይረጭ ነበር።

[22] ደግሞም በቀረበው ሁሉ እንዲህ ያደርግ ነበር፥ በኦሪት ሕግ ሁሉ በደም ይነጻ ነበር፤ ደም ሳይረጭ ግን አይሰረይም ነበር።

[23] በሰማይ ባለው አምሳል የተሠራው ይህ ሥራ፥ በዚህ ደም የሚነጻ ከሆነ፥ ይህ ሰማያዊ መሥዋዕትስ ከዚህ ይበልጣል።

[24] ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ፥ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።

[25] ሊቀ ካህናቱ ያደርገው እንደ ነበረ፥ በያመቱም ደም ይዞ ወደ ቅድስት ይገባ እንደ ነበረ ዘወትር ራሱን የሚሠዋ አይደለም።

[26] ይህስ ባይሆን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ በሞተ ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ፥ ራሱን በመሠዋት ኀጢአትን ይሽራት ዘንድ አንድ ጊዜ ተገለጠ።

[27] ለሰው አንድ ጊዜ ሞት፥ ከዚያም በኋላ ፍርድ እንደሚጠብቀው፥

[28] እንዲሁ ክርስቶስም የብዙዎችን ኀጢአት ያስተሰርይ ዘንድ ራሱን አንድ ጊዜ ሠዋ፤ በኋላ ግን ያድናቸው ዘንድ ተስፋ ለሚያደርጉት ያለ ኀጢአት ይገለጥላቸዋል።

ወደ ዕብራውያን — Chapters