Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:59

[1] እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ፥ የኀጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ።

[2] የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው፤ እርሱ ነውርን ንቆ፥ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።

[3] በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኀጢአተኟች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን እስኪ ዐስቡት።

[4] ገና አልጸናችሁምና ደማችሁን ለማፍሰስ እስክትደርሱ ኀጢአትን ተጋደሉኣት፥ አሸንፉኣትም፤ ተስፋችሁን የምታገኙባትን ትምህርትም ውደዷት።

[5] እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር ፥ “ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም።

[6] እግዚአብሔር የሚወደውን ይገሥጻልና፥ የሚወደደውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ” ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል።

[7] ቅጣታችሁን ታገሡ፤ ልጆቹ እንደ መሆናችሁ ይወዳችኋልና፤ አባቱ የማይቈጣው ልጅ ማን ነው?

[8] ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና፥ ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም።

[9] በሥጋ የወለዱን አባቶቻችን የሚቀጡን፥ እኛም የምንፈራቸው ከሆነ፥ እንግዲያ ይልቁን ለመንፈስ አባታችን ልንታዘዝና ልንገዛ በሕይወትም ልንኖር እንዴት ይገባን ይሆን?

[10] እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡናል፤ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል።

[11] ቅጣት ሁሉ በጊዜው ያሳዝናል እንጂ ደስ አያሰኝም፤ በኋላ ግን ለተቀጡ ሰላምን ያፈራል፤ ጽድቅንም ያሰጣቸዋል።

[12] ስለዚህም የላሉትን እጆች፥ የሰለሉትንም ጕuልበቶች አቅኑ።

[13] አንካሳነታችሁ እንዲድንና እንዳትሰነካከሉ ለእግሮቻችሁ የቀና መንገድን አድርጉ።

[14] ከሁሉ ጋር ወደ ሰላም ሩጡ፤ ቅድስናችሁንም አትተዉ፤ ያለ እርሱ ግን እግዚአብሔርን የሚያየው የለም።

[15] አስተውሉ፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ የሚያቃልል አይኑር፤ ሕማምን የምታመጣ፥ ብዙዎችንም የምታስታቸውና የምታረክሳቸው መራራ ሥር የምትገኝበትም አይኑር።

[16] ለጥቂት መብል ብኵuርናውን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ሴሰኛና ርኩስ የሚሆን አይኑር።

[17] ከዚያ በኋላ እንኳ በረከትን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባም ተግቶ ምንም ቢፈልጋት ለንስሓ ስፍራ አላገኘምና።

[18] ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም፥ ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም፥

[19] ወደ መለከት ድምፅም፥ ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና፥ ያንም ነገር የሰሙት ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው ለመኑ።

[20] የተነጋገራቸውን ሊሰሙት አልተቻላቸውም ነበርና፥ “እንስሳም ያን ተራራ ቢቀርበው በድንጋይ ይወግሩት ” ነበር።

[21] የታያቸውም እንዲህ ግሩም ነበር፤ ሙሴም እንኳን ፥ “እኔ ፈርቻለሁ፥ ደንግጫለሁም ” አለ።

[22] እናንተ ግን፥ የሕያው እግዚአብሔር ከተማ ወደምትሆን ወደ ጽዮን ተራራ፥ በሰማያት ወደ አለችው ኢየሩሳሌም፥ ደስ ብሎአቸው ወደሚኖሩ አእላፍ መላእክትም ደርሳችኋል።

[23] ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈ ወደ ማኅበረ በኵuርም፥ ሁሉን ወደሚገዛም ወደ እግዚአብሔር፥ ወደ ፍጹማን ጻድቃንም ነፍሳት፥

[24] የአዲስ ኪዳንም መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ ተረጨው ደሙ ደርሳችኋል።

[25] ለሚናገረው እንቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነርሱ በደብረ ሲና የተገለጠላቸውን እንቢ ስለ አሉት ካልዳኑ፥ ከሰማይ ከመጣው ፊታችንን ብንመልስ እኛማ እንዴታ?

[26] ያንጊዜ ቃል ምድርን አናወጣት፤ “አሁንም እኔ ምድርን እንደ ገና አንድ ጊዜ አናውጣታለሁ ” ብሎ ተናገረ፤ ምድርን ብቻም አይደለም፤ ሰማይንም ጭምር እንጂ።

[27] አንድ ጊዜ ደግሞ ያለውም ፍጡራን ናቸውና፥ የማይናወጠው ይኖር ዘንድ፥ የሚናወጠውን እንደሚያሳልፈው ያሳያል።

[28] ስለዚህ የማይናወጥ መንግሥትን ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሀት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ።

[29] አምላካችን በእውነት የሚያቃጥል እሳት ነውና።

ወደ ዕብራውያን — Chapters