Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:55

[1] እንግዲህ አንፍራ፤ ወደ ዕረፍቱም እንድንገባ ትእዛዙን አንተው፤ ከእናንተም ምንአልባት በተለመደ ስሕተት የሚገኝና የሚጸና ቢኖር ወደ ዕረፍቱ እንዲገባ የሚተዉት አይምሰለው።

[2] ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛም የምሥራች ተሰብኮልናል፤ ነገር ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።

[3] ሥራዉ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም ፥ “እንግዲህ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቐጣዬ ማልሁ ” እንዳለ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን።

[4] ስለ ሰባተኛውም ቀን ፥ “እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ ” ብሎአልና።

[5] ዳግመኛም ፥ “ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ” ብሎአል።

[6] እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ መንገድ ስለ ነበራቸው ቀድሞም የምሥራች የተሰበከላቸው ባለ መታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ ፥

[7] “ዛሬ ቃሉን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ፤” በፊት እንደ ተባለ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር ፥ “ዛሬ ” ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል።

[8] ኢያሱ አሳርፎአቸው ቢሆን ኖሮስ፥ ከብዙ ዘመን በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረም ነበር።

[9] እንኪያስ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚገቡበት ጸንቶ የሚኖር ዕረፍት እንዳለ ታወቀ።

[10] ወደ ዕረፍቱ የገባስ እግዚአብሔር ከሥራው እንደ ዐረፈ፥ እነሆ፥ እርሱ ከሥራው ሁሉ ዐረፈ።

[11] እንግዲህ እንደ እነዚያ እንደ ካዱት እንዳንወድቅ፥ ወደ ዕረፍቱ እንገባ ዘንድ እንፋጠን።

[12] የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፤ የሚሠራም ሁለት ልሳን ካለው ሰይፍም ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም፥ ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።

[13] እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ በዐይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።

[14] እንግዲህ ወደ ሰማያት የወጣ ታላቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፤ በእርሱ በማመን ጸንተን እንኑር።

[15] ሊቀ ካህናታችን ለድካማችን መከራ መቀበልን የማይችል አይደለምና፤ ነገር ግን ከብቻዋ ከኀጢአት በቀር እኛን በመሰለበት ሁሉ የተፈተነ ነው።

[16] እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል፥ በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፥ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።

ወደ ዕብራውያን — Chapters