[1] አሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት በአንድነት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤
[2] የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ ላካቸው፥
[3] እንዲህም አላቸው። በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን ለመንገድ ምንም አትያዙ፥ ሁለት እጀ ጠባብም አይሁንላችሁ።
[4] በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ ከዚያም ውጡ።
[5] ማናቸውም የማይቀበሉአችሁ ቢሆኑ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያ አራግፉ።
[6] ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በስፍራው ሁሉ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።
[7] የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ አንዳንድ ሰዎች።
[8] ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፥ ሌሎችም። ኤልያስ ተገለጠ፥ ሌሎችም። ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይሉ ስለ ነበሩ አመነታ።
[9] ሄሮድስም። ዮሐንስንስ እኔ ራሱን አስቈረጥሁት፤ ይህ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ማን ነው? አለ። ሊያየውም ይሻ ነበር።
[10] ሐዋርያትም ተመልሰው ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። ከእርሱ ጋርም ወስዶአቸው ቤተ ሳይዳ ከምትባል ከተማ አጠገብ ወደ ምድረ በዳ ለብቻው ፈቀቅ አለ።
[11] ሕዝቡም አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፥ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው።
[12] ቀኑም ይመሽ ጀመር፤ አሥራ ሁለቱም ቀርበው። በዚህ በምድረ በዳ ነንና በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩና ምግብ እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት።
[13] እርሱ ግን። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። እነርሱም። ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን፥ ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ የሚበልጥ የለንም አሉት፤
[14] አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና። ለደቀ መዛሙርቱ። በየክፍሉ አምሳ አምሳውን አስቀምጡአቸው አላቸው።
[15] እንዲህም አደረጉ ሁሉንም አስቀመጡአቸው።
[16] አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛርሙርቱ ሰጠ።
[17] ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ ከእነርሱም የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ወሰዱ።
[18] ለብቻውም ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና። ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ጠየቃቸው።
[19] እነርሱም መልሰው። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም። ኤልያስ፥ ሌሎችም። ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይላሉ አሉት።
[20] እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ። ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ አለ።
[21] -
[22] እርሱ ግን። የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል በሽማግሌዎችም በካህናት አለቆችም በጻፎችም ሊጣል ሊገደልም በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባዋል ብሎ ለማንም ይህን እንዳይናገሩ አስጠንቅቆ አዘዘ።
[23] ለሁሉም እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።
[24] ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል።
[25] ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?
[26] በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ በእርሱ ያፍርበታል።
[27] እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።
[28] ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ።
[29] ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ።
[30] እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤
[31] በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።
[32] ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ።
[33] ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን። አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር።
[34] ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ።
[35] ከደመናውም። የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።
[36] ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም።
[37] በነገውም ከተራራ ሲወርዱ ብዙ ሕዝብ ተገናኙት።
[38] እነሆም፥ ከሕዝቡ አንድ ሰው እንዲህ እያለ ጮኸ። መምህር ሆይ፥ ለእኔ አንድ ልጅ ነውና ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ።
[39] እነሆም፥ ጋኔን ይይዘዋል፥ ድንገትም ይጮኻል አረፋም እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፥ እየቀጠቀጠም በጭንቅ ይለቀዋል፤
[40] ደቀ መዛሙርትህንም እንዲያወጡት ለመንሁ፥ አልቻሉምም።
[41] ኢየሱስም መልሶ። እናንተ የማታምን ጠማማ ትውልድ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው አለ።
[42] ሲቀርብም ጋኔኑ ጣለውና አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኵሱን መንፈስ ገሥጾ ብላቴናውን ፈወሰው ለአባቱም መለሰው።
[43] ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ ተገረሙ። ሁሉም ኢየሱስ ባደረገው ሁሉ ሲደነቁ፥
[44] ለደቀ መዛሙርቱ። የሰው ልጅ በሰው እጅ ይሰጥ ዘንድ አለውና እናንተ ይህን ቃል በጆሮአችሁ አኑሩ አለ።
[45] እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉም፥ እንዳይገባቸውም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህ ነገርም እንዳይጠይቁት ፈሩ።
[46] ከእነርሱም ማን እንዲበልጥ ክርክር ተነሣባቸው።
[47] ኢየሱስም የልባቸውን አሳብ አውቆ ሕፃንን ያዘ፤ በአጠገቡም አቁሞ።
[48] ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና አላቸው።
[49] ዮሐንስም መልሶ። አቤቱ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፥ ከእኛ ጋርም ስለማይከተል ከለከልነው አለው።
[50] ኢየሱስ ግን። የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነውና አትከልክሉት አለው።
[51] የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፥
[52] በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ፤
[53] ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለ ነበረ አልተቀበሉትም።
[54] ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው። ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? አሉት።
[55] እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና። ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ሆነላችሁ አታውቁም፤
[56] የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።
[57] እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው። ጌታ ሆይ፥ ወደ ምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው።
[58] ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው።
[59] ሌላውንም። ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ አለ።
[60] ኢየሱስም። ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ አለው።
[61] ደግሞ ሌላው። ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ።
[62] ኢየሱስ ግን። ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው።