Skip to content
Opens in a new window

[1] ሁሉም በሞላው ተነሥተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱትና።

[2] ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም። እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር።

[3] ጲላጦስም። አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም መልሶ። አንተ አልህ አለው።

[4] ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ። በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም አለ።

[5] እነርሱ ግን አጽንተው። ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በይሁዳ ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል አሉ።

[6] ጲላጦስ ግን። ገሊላ ሲሉ በሰማ ጊዜ። የገሊላ ሰው ነውን? ብሎ ጠየቀ፤

[7] ከሄሮድስም ግዛት እንደ ሆነ ባወቀ ጊዜ ወደ ሄሮድስ ሰደደው፤ እርሱ ደግሞ በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም ነበረና።

[8] ሄሮድስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ስለ ሰማ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይመኝ ነበርና፥ ምልክትም ሲያደርግ ሊያይ ተስፋ ያደርግ ነበር።

[9] በብዙ ቃልም ጠየቀው፤ እርሱ ግን አንድ ስንኳ አልመለሰለትም።

[10] የካህናት አለቆችና ጻፎችም አጽንተው ሲከሱት ቆመው ነበር።

[11] ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር ናቀው ዘበተበትም፥ የጌጥ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው።

[12] ሄሮድስና ጲላጦስም በዚያን ቀን እርስ በርሳቸው ወዳጆች ሆኑ፥ ቀድሞ በመካከላቸው ጥል ነበረና።

[13] ጲላጦስም፥ የካህናትን አለቆችና መኳንንትን ሕዝቡንም በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው።

[14] ሕዝቡን ያጣምማል ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እነሆም፥ በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል ስንኳ በዚህ ሰው አላገኘሁበትም።

[15] ሄሮድስም ደግሞ ምንም አላገኘም፤ ወደ እኛ መልሶታልና፤ እነሆም፥ ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም፤

[16] -

[17] እንግዲያስ ቀጥቼ እፈታዋለሁ። በበዓሉ አንድ ይፈታላቸው ዘንድ ግድ ነበረና።

[18] ሁላቸውም በአንድነት። ይህን አስወግድ፥ በርባንንም ፍታልን እያሉ ጮኹ፤

[19] እርሱም ሁከትን በከተማ አንሥቶ ሰውን ስለ ገደለ በወኅኒ ታስሮ ነበር።

[20] ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታ ወድዶ ዳግመኛ ተናገራቸው፤

[21] ነገር ግን እነርሱ። ስቀለው ስቀለው እያሉ ይጮኹ ነበር።

[22] ሦስተኛም። ምን ነው? ያደረገውስ ክፋት ምንድር ነው? ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ አላቸው።

[23] እነርሱ ግን እንዲሰቀል በታላቅ ድምፅ አጽንተው ለመኑት። የእነርሱ ጩኸትና የካህናት አለቆችም ቃል በረታ።

[24] ጲላጦስም ልመናቸው እንዲሆንላቸው ፈረደበት።

[25] ያንን የለመኑትንም፥ ስለ ሁከት ሰውንም ስለ መግደል በወኅኒ ታስሮ የነበረውን አስፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጠው።

[26] በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ ይዘው ከኢየሱስ በኋላ መስቀሉን እንዲሸከም ጫኑበት።

[27] ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት።

[28] -

[29] ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ። እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን። መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ።

[30] በዚያን ጊዜ ተራራዎችን። በላያችን ውደቁ፥ ኮረብቶችንም። ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ፤

[31] በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ እንዴት ይሆን?

[32] ሌሎችንም ሁለት ክፉ አድራጊዎች ደግሞ ከእርሱ ጋር ይገድሉ ዘንድ ወሰዱ።

[33] ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ።

[34] ኢየሱስም። አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት።

[35] ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኳንንቱም ደግሞ። ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን እያሉ ያፌዙበት ነበር።

[36] ጭፍሮችም ደግሞ ወደ እርሱ ቀርበው ሆምጣጤም አምጥተው።

[37] አንተስ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን እያሉ ይዘብቱበት ነበር።

[38] ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው ተብሎ በግሪክና በሮማይስጥ በዕብራይስጥም ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ።

[39] ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ። አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው።

[40] ሁለተኛው ግን መልሶ። አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን?

[41] ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው።

[42] ኢየሱስንም። ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው።

[43] ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።

[44] ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥

[45] የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ።

[46] ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ። አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ።

[47] የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ።

[48] ይህንም ለማየት ተከማችተው የነበሩ ሕዝብ ሁሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ።

[49] የሚያውቁቱ ግን ሁሉ ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ይህን እያዩ በሩቅ ቆመው ነበር።

[50] እነሆም፥ በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ አማካሪም የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤

[51] ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር።

[52] ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤

[53] አውርዶም በተልባ እግር ልብስ ከፈነው፥ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው።

[54] የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም ሊጀምር ነበረ።

[55] ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ።

[56] ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ።

የሉቃስ ወንጌል። — Chapters