[1] ከዚህም በኋላ እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ ነበር፤
[2] አሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፥
[3] የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር።
[4] ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ ከከተማዎችም ሁሉ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በምሳሌ እንዲህ ሲል ተናገራቸው።
[5] ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ ተረገጠም፥ የሰማይ ወፎችም በሉት።
[6] ሌላውም በዓለት ላይ ወደቀ፥ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ።
[7] ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው።
[8] ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ። ይህን በተናገረ ጊዜ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ብሎ ጮኸ።
[9] ደቀ መዛሙርቱም። ይህ ምሳሌ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት።
[10] እርሱም እንዲህ አለ። ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው።
[11] ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው።
[12] በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።
[13] በዓለት ላይም ያሉት ሲሰሙ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው።
[14] በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም።
[15] በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።
[16] መብራትንም አብርቶ በዕቃ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ።
[17] የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም።
[18] እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፥ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።
[19] እናቱና ወንድሞቹም ወደ እርሱ መጡ፥ ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ሊያገኙት አልተቻላቸውም።
[20] እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ወድደው በውጭ ቆመዋል ብለው ነገሩት።
[21] እርሱም መልሶ። እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው አላቸው።
[22] ከዕለታቱም በአንዱ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ። ወደ ባሕር ማዶ እንሻገር አላቸው፤ ተነሡም።
[23] ሲሄዱም አንቀላፋ። ዓውሎ ነፋስም በባሕር ላይ ወረደ፥ ውኃውም ታንኳይቱን ይሞላ ነበርና ይጨነቁ ነበር።
[24] ቀርበውም። አቤቱ፥ አቤቱ ጠፋን እያሉ አስነሡት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውኃውን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ተዉም፥ ጽጥታም ሆነ።
[25] እርሱም። እምነታችሁ የት ነው? አላቸው። ፈርተውም ተደነቁ፥ እርስ በርሳቸውም። እንዲህ ነፋሳትንና ውኃን እንኳ የሚያዝ ለእርሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? አሉ።
[26] በገሊላም አንጻር ወዳለችው ወደ ጌርጌሴኖን አገር በታንኳ ደረሱ።
[27] ወደ ምድርም በወጣ ጊዜ አጋንንት ያደሩበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ ተገናኘው፥ ከብዙ ዘመንም ጀምሮ ልብስ ሳይለብስ በመቃብር እንጂ በቤት አይኖርም ነበር።
[28] ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ በታላቅ ድምፅም። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቀየኝ እለምንሃለሁ አለ።
[29] ርኵሱን መንፈስ ከሰውዬው እንዲወጣ ያዘው ነበርና። ብዙ ዘመንም ይዞት ነበርና፥ በሰንሰለትና በእግር ብረትም ታስሮ ይጠበቅ ነበር፤ እስራቱንም ሰብሮ በጋኔኑ ወደ ምድረ በዳ ይነዳ ነበር።
[30] ኢየሱስም። ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙዎች አጋንንት ገብተውበት ነበርና። ሌጌዎን አለው።
[31] ወደ ጥልቁም ሊሄዱ እንዳያዛቸው ለመኑት።
[32] በዚያም በተራራው የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማሩ ነበር፤ ወደ እነርሱም ሊገቡ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ ፈቀደላቸውም።
[33] አጋንንትም ከሰውዬው ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፥ መንጋውም ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና ሰጠሙ።
[34] እረኞችም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩት።
[35] የሆነውን ነገር ሊያዩ ወጥተውም ወደ ኢየሱስ መጡ፥ አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ ልቡም ተመልሶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ።
[36] ያዩትም ደግሞ አጋንንት ያደሩበት ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው።
[37] በዙሪያውም በጌርጌሴኖን አገር ያሉት ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ይዞአቸዋልና ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት በታንኳም ገብቶ ተመለሰ።
[38] አጋንንት የወጡለት ሰውም ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ ለመነው፤
[39] ነገር ግን። ወደ ቤትህ ተመለስ፥ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረግልህ ንገር ብሎ አሰናበተው። ኢየሱስም እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት በከተማው ሁሉ እየሰበከ ሄደ።
[40] ኢየሱስም በተመለሰ ጊዜ ሁሉ ይጠብቁት ነበርና ሕዝቡ ተቀበሉት።
[41] እነሆም፥ ኢያኢሮስ የሚባል ሰው መጣ፥ እርሱም የምኵራብ አለቃ ነበረ በኢየሱስም እግር ላይ ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲገባ ለመነው፤
[42] አሥራ ሁለት ዓመት የሆናት አንዲት ሴት ልጅ ነበረችውና፤ እርስዋም ለሞት ቀርባ ነበረች። ሲሄድም ሕዝቡ ያጨናንቁት ነበር።
[43] ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ትዳርዋንም ሁሉ ለባለመድኃኒቶች ከስራ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም።
[44] በኋላውም ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፥ የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ።
[45] ኢየሱስም። የዳሰሰኝ ማን ነው? አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፥ ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር የነበሩት። አቤቱ፥ ሕዝቡ ያጫንቁሃልና ያጋፉህማል፤ የዳሰሰኝ ማን ነው ትላለህን? አሉ።
[46] ኢየሱስ ግን። አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና አለ።
[47] ሴቲቱም እንዳልተሰወረች ባየች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፥ በምን ምክንያትም እንደ ዳሰሰችው ፈጥናም እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት አወራች።
[48] እርሱም። ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።
[49] እርሱም ገና ሲናገር አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ቤት መጥቶ። ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህሩን አታድክም አለ።
[50] ኢየሱስ ግን ሰምቶ። አትፍራ፤ እመን ብቻ ትድንማለች ብሎ መለሰለት።
[51] ወደ ቤትም ሲገባ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ ከዮሐንስም ከብላቴናይቱም አባትና እናት በቀር ማንም ከእርሱ ጋር ይገባ ዘንድ አልፈቀደም።
[52] ሁሉም እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን። አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አለ።
[53] እንደ ሞተችም አውቀው በጣም ሳቁበት።
[54] እርሱ ግን እጅዋን ይዞ። አንቺ ብላቴና፥ ተነሺ ብሎ ጮኸ።
[55] ነፍስዋም ተመለሰች፥ ፈጥናም ቆመች፥ የምትበላውንም እንዲሰጡአት አዘዘ።
[56] ወላጆችዋም ተገረሙ፤ እርሱ ግን የሆነውን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው።