[1] ቀራጮችና ኃጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር።
[2] ፈሪሳውያንና ጻፎችም። ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል ብለው እርስ በርሳቸው አንጐራጐሩ።
[3] ይህንም ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል።
[4] መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው?
[5] ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤
[6] ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ። የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል።
[7] እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።
[8] ወይም አሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፥ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት?
[9] ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ። የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ትላቸዋለች።
[10] እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።
[11] እንዲህም አለ። አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት።
[12] ከእነርሱም ታናሹ አባቱን። አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው።
[13] ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገዘቡን በተነ።
[14] ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር።
[15] ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው።
[16] እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም።
[17] ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ። እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ።
[18] ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥
[19] ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ።
[20] ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው።
[21] ልጁም። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው።
[22] አባቱ ግን ባሪያዎቹን አለ። ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤
[23] የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤
[24] ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር።
[25] ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የመሰንቆና የዘፈን ድምፅ ሰማ፤
[26] ከብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ። ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ።
[27] እርሱም። ወንድምህ መጥቶአልና በደኅና ስላገኘው አባትህ የሰባውን ፊሪዳ አረደለት አለው።
[28] ተቈጣም ሊገባም አልወደደም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው።
[29] እርሱ ግን መልሶ አባቱን። እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጥቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤
[30] ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፊሪዳ አረድህለት አለው።
[31] እርሱ ግን። ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፥ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤
[32] ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል አለው።