[1] በሰንበትም ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት እንጀራ ሊበላ በገባ ጊዜ እነርሱ ይጠባበቁት ነበር።
[2] እነሆም፥ ሆዱ የተነፋ ሰው በፊቱ ነበረ።
[3] ኢየሱስም መልሶ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? ብሎ ለሕግ አዋቂዎችና ለፈሪሳውያን ተናገረ።
[4] እነርሱ ግን ዝም አሉ። ይዞም ፈወሰውና አሰናበተው።
[5] ከእናንተ አህያው ወይስ በሬው በጕድጓድ ቢወድቅ በሰንበት ወዲያው የማያወጣው ማን ነው? አላቸው።
[6] ስለዚህ ነገርም ሊመልሱለት አልተቻላቸውም።
[7] የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል።
[8] ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና አንተን እርሱንም የጠራ መጥቶ።
[9] ለዚህ ስፍራ ተውለት ይልሃል፥ በዚያን ጊዜም እያፈርህ በዝቅተኛው ስፍራ ልትሆን ትጀምራለህ።
[10] ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ፥ የጠራህ መጥቶ። ወዳጄ ሆይ፥ ወደ ላይ ውጣ እንዲልህ፥ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል።
[11] ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።
[12] የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው። ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለ ጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ።
[13] ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤
[14] የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና።
[15] ከተቀመጡትም አንዱ ይህን ሰምቶ። በእግዚአብሔር መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ ነው አለው።
[16] እርሱ ግን እንዲህ አለው። አንድ ሰው ታላቅ እራት አድርጎ ብዙዎችን ጠራ፤
[17] በእራትም ሰዓት የታደሙትን። አሁን ተዘጋጅቶአልና ኑ እንዲላቸው ባሪያውን ላከ።
[18] ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የፊተኛው። መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው።
[19] ሌላውም። አምስት ጥምድ በሬዎች ገዝቼአለሁ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው።
[20] ሌላውም። ሚስት አግብቼአለሁ ስለዚህም ልመጣ አልችልም አለው።
[21] ባሪያውም ደርሶ ይህን ለጌታው ነገረው። በዚያን ጊዜ ባለቤቱ ተቆጥቶ ባሪያውን። ወደ ከተማ ጎዳናና ወደ ስላች ፈጥነህ ውጣ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንና ዕውሮችንም ወደዚህ አግባ አለው።
[22] ባሪያውም። ጌታ ሆይ፥ እንዳዘዝኸኝ ተደርጎአል፥ ገናም ስፍራ አለ አለው።
[23] ጌታውም ባሪያውን። ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው፤
[24] እላችኋለሁና፥ ከታደሙት ከእነዚያ ሰዎች አንድ ስንኳ እራቴን አይቀምስም አለው።
[25] ብዙም ሕዝብ ከእርሱ ጋር ይሄዱ ነበር፥ ዘወር ብሎም እንዲህ አላቸው።
[26] ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
[27] ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
[28] ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቈጥር ማን ነው?
[29] ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፥ ሊደመድመውም ቢያቅተው፥ ያዩት ሁሉ።
[30] ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ።
[31] ወይም ሌላውን ንጉሥ በጦርነት ሊጋጠም የሚሄድ፥ ከሁለት እልፍ ጋር የሚመጣበትን በአንድ እልፍ ሊገናኝ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ንጉሥ ማን ነው?
[32] ባይሆንስ ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልክተኞች ልኮ ዕርቅ ይለምናል።
[33] እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
[34] ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፈጣል?
[35] ለምድር ቢሆን ለፍግ መቈለያም ቢሆን አይረባም፤ ወደ ውጭ ይጥሉታል። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።