Skip to content
Opens in a new window

[1] -

[2] ወደ ኢያሪኮም ገብቶ ያልፍ ነበር። እነሆም ዘኬዎስ የሚባል ሰው፥ እርሱም የቀራጮች አለቃ ነበረ፥ ባለ ጠጋም ነበረ።

[3] ኢየሱስንም የትኛው እንደ ሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ስለ ሕዝቡ ብዛት አቃተው።

[4] በዚያችም መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና ያየው ዘንድ ወደ ፊት ሮጦ በአንድ ሾላ ላይ ወጣ።

[5] ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና። ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው።

[6] ፈጥኖም ወረደ በደስታም ተቀበለው።

[7] ሁሉም አይተው። ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ።

[8] ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን። ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው።

[9] ኢየሱስም። እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤

[10] የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው።

[11] እነርሱም ይህን ሲሰሙ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መቅረቡ ስለ ሆነ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለ መሰላቸው ምሳሌ ጭምር ተናገረ።

[12] ስለዚህም እንዲህ አላቸው። አንድ መኰንን ለራሱ መንግሥትን ይዞ ሊመለሰ ወደ ሩቅ አገር ሄደ።

[13] አሥር ባሪያዎችንም ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና። እስክመጣ ድረስ ነግዱ አላቸው።

[14] የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና። ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም ብለው በኋላው መልክተኞችን ላኩ።

[15] መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፥ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ እንዲጠሩለት አዘዘ።

[16] የፊተኛውም ደርሶ። ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አሥር ምናን አተረፈ አለው።

[17] እርሱም። መልካም፥ አንተ በጎ ባሪያ፥ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በአሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ይሁንልህ አለው።

[18] ሁለተኛውም መጥቶ። ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አምስት ምናን አተረፈ አለው።

[19] ይህንም ደግሞ። አንተም በአምስት ከተማዎች ላይ ሁን አለው።

[20] ሌላውም መጥቶ። ጌታ ሆይ፥ በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤

[21] ፈርቼሃለሁና፥ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ፤ ያላኖርኸውን ትወስዳለህ ያልዘራኸውንም ታጭዳለህ አለው።

[22] እርሱም። አንተ ክፉ ባሪያ፥ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላኖርሁትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ አወቅህ፤ ምን ነው ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው?

[23] እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር አለው።

[24] በዚያም ቆመው የነበሩትን። ምናኑን ውሰዱበት አሥሩ ምናን ላለውም ስጡት አላቸው።

[25] እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ አሥር ምናን አለው አሉት።

[26] እላችኋለሁ፥ ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፥ ከሌለው ግን ያው ያለው ስንኳ ይወሰድበታል።

[27] ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው።

[28] ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር።

[29] ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና።

[30] በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፥ ፈትታችሁም አምጡት።

[31] ማንም። ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ እንዲሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉ አላቸው።

[32] የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ።

[33] እነርሱም ውርንጫውን ሲፈቱ ጌቶቹ። ውርንጫውን ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? አሉአቸውም

[34] እነርሱም። ለጌታ ያስፈልገዋል አሉ።

[35] ወደ ኢየሱስም አመጡት፥ በውርንጫውም ላይ ልብሳቸውን ጭነው ኢየሱስን አስቀመጡት።

[36] ሲሄድም ልብሳቸውን በመንገድ ያነጥፉ ነበር።

[37] ወደ ደብረ ዘይት ቍልቍለትም አሁን በቀረበ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሁላቸው ደስ እያላቸው ተአምራትን ሁሉ ስላዩ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ ጀምረው።

[38] በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው፤ በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር አሉ።

[39] ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ። መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት።

[40] መልሶም። እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው።

[41] ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥

[42] እንዲህ እያለ። ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል።

[43] ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤

[44] አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።

[45] ወደ መቅደስም ገብቶ በእርሱ የሚሸጡትን የሚገዙትንም ያወጣ ጀመር፤

[46] እርሱም። ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት አላቸው።

[47] ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች የሕዝቡ ታላላቆችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፥

[48] የሚያደርጉበትንም አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት ነበርና።

የሉቃስ ወንጌል። — Chapters