[1] ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃል እየሰሙ ሲያስጠብቡት ሳሉ፥ እርሱ ራሱ በጌንሳሬጥ ባሕር ዳር ቆሞ ነበር፤
[2] በባሕር ዳርም ቆመው የነበሩትን ሁለት ታንኳዎች አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ግን ከእነርሱ ውስጥ ወጥተው መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር።
[3] ከታንኳዎቹም የስምዖን ወደ ነበረች ወደ አንዲቱ ገብቶ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ በታንኳይቱም ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ነበር።
[4] ነገሩንም ከጨረሰ በኋላ፥ ስምዖንን። ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ አለው።
[5] ስምዖንም መልሶ። አቤቱ፥ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ አለው።
[6] ይህንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረቦቻቸውም ተቀደዱ።
[7] በሌላ ታንኳም የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው ጠቀሱ፤ መጥተውም ሁለቱ ታንኳዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው።
[8] ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ። ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ አለው።
[9] ስላጠመዱት ዓሣ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩ ሁሉ ተደንቀዋልና፥
[10] እንዲሁም ደግሞ የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ። ኢየሱስም ስምዖንን። አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ አለው።
[11] ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት።
[12] ከከተማዎችም በአንዲቱ ሳለ፥ እነሆ፥ ለምጽ የሞላበት ሰው ነበረ፤ ኢየሱስንም አይቶ በፊቱ ወደቀና። ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ፥ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው።
[13] እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ለቀቀው።
[14] እርሱም ለማንም እንዳይናገር አዘዘው፥ ነገር ግን። ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ እንዳዘዘ መሥዋዕት አቅርብ አለው።
[15] ወሬው ግን አብዝቶ ወጣ፥ ብዙ ሕዝብም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ይሰበሰቡ ነበር፤
[16] ነገር ግን እርሱ ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ ብሎ ይጸልይ ነበር።
[17] አንድ ቀንም ያስተምር ነበር፤ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮችም ሁሉ ከኢየሩሳሌምም መጥተው የነበሩ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ይቀመጡ ነበር፤ እርሱም እንዲፈውስ የጌታ ኃይል ሆነለት።
[18] እነሆም፥ አንድ ሽባ በአልጋ ተሸክመው አመጡ፤ አግብተውም በፊቱ ሊያኖሩት ይሹ ነበር።
[19] ስለ ሕዝቡም ብዛት እንዴት አድርገው እንዲያገቡት ሲያቅታቸው፥ ወደ ሰገነቱ ወጡ የጣራውንም ጡብ አሳልፈው በመካከል በኢየሱስ ፊት ከነአልጋው አወረዱት።
[20] እምነታቸውንም አይቶ። አንተ ሰው፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው።
[21] ጻፎችና ፈሪሳውያንም። ይህ የሚሳደብ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው ያስቡ ጀመር።
[22] ኢየሱስም አሳባቸውን እያወቀ መልሶ። በልባችሁ ምን ታስባላችሁ?
[23] ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?
[24] ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአት ሊያስተሰርይ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ብሎ፥ ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ነተሣ፥ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ አለው።
[25] በዚያን ጊዜም በፊታቸው ተነሣ፥ ተኝቶበትም የነበረውን ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ።
[26] ሁሉንም መገረም ያዛቸው፥ እግዚአብሔርንም አመስግነው። ዛሬስ ድንቅ ነገር አየን እያሉ ፍርሃት ሞላባቸው።
[27] ከዚህም በኋላ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ በመቅረጫው ተቀምጦ ተመለከተና። ተከተለኝ አለው።
[28] ሁሉንም ተወ፤ ተነሥቶም ተከተለው።
[29] ሌዊም በቤቱ ታላቅ ግብዣ አደረገለት፤ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩ ከቀራጮችና ከሌሎች ሰዎች ብዙ ሕዝብ ነበሩ።
[30] ፈሪሳውያንና ጻፎቻቸውም በደቀ መዛሙርቱ ላይ። ስለ ምን ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ትበላላችሁ ትጠጡማላችሁ? ብለው አንጐራጐሩ።
[31] ኢየሱስም መልሶ። ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤
[32] ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።
[33] እነርሱም። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለ ምን ብዙ ይጦማሉ ጸሎትስ ስለ ምን ያደርጋሉ፥ ደግሞም የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ስለ ምን እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ይበላሉ ይጠጣሉም? አሉት።
[34] ኢየሱስም። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎችን ልታስጦሙ ትችላላችሁን?
[35] ነገር ግን ወራት ይመጣል፥ ሙሽራውም ከእነርሱ ሲወሰድ ያንጊዜ፥ በዚያ ወራት ይጦማሉ አላቸው።
[36] ደግሞም ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው። የአዲስ ልብስ እራፊ ባረጀ ልብስ ላይ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱን ይቀደዋል ደግሞም አዲስ እራፊ ለአሮጌው አይስማማውም።
[37] ባረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳል፥ እርሱም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል።
[38] አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።
[39] አሮጌ የወይን ጠጅ ሲጠጣ አዲሱን የሚሻ ማንም የለም፤ አሮጌው ይጣፍጣል ይላልና።