[1] ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፤ እርሱም የጥብርያዶስ ባሕር ነው።
[2] በበሽተኞችም ያደረገውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።
[3] ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።
[4] የአይሁድ በዓልም ፋሲካ ቀርቦ ነበር።
[5] ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን። እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን? አለው።
[6] ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ይህን ተናገረ።
[7] ፊልጶስ። እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት።
[8] ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ።
[9] አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል? አለው።
[10] ኢየሱስም። ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ አለ። በዚያም ስፍራ ብዙ ሣር ነበረበት። ወንዶችም ተቀመጡ ቍጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር።
[11] ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፥ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን።
[12] ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን። አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ አከማቹ አላቸው።
[13] ሰለዚህ አከማቹ፥ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ።
[14] ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ። ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው አሉ።
[15] በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ።
[16] በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፥
[17] በታንኳም ገብተው በባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር። አሁንም ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር፤
[18] ብርቱ ነፋስም ስለ ነፈሰ ባሕሩ ተናወጠ።
[19] ሀያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ከቀዘፉ በኋላም፥ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ ታንኳይቱ ሲቀርብ አይተው ፈሩ።
[20] እርሱ ግን። እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው።
[21] ስለዚህ በታንኳይቱ ሊቀበሉት ወደዱ፤ ወዲያውም ታንኳይቱ ወደሚሄዱበት ምድር ደረሰች።
[22] በነገው በባሕር ማዶ ቆመው የነበሩ ሕዝቡ ከአንዲት ጀልባ በቀር በዚያ ሌላ ጀልባ እንዳልነበረች፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ አዩ፤
[23] ዳሩ ግን ሌሎች ጀልባዎች ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አጠገብ ከጥብርያዶስ መጡ።
[24] ሕዝቡም ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ፥ ራሳቸው በጀልባዎቹ ገብተው ኢየሱስን እየፈለጉ ወደ ቅፍርናሆም መጡ።
[25] በባሕር ማዶም ሲያገኙት። መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ? አሉት።
[26] ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም።
[27] ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።
[28] እንግዲህ። የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት።
[29] ኢየሱስ መልሶ። ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው።
[30] እንግዲህ። እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ?
[31] ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ አሉት።
[32] ኢየሱስም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤
[33] የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው።
[34] ስለዚህ። ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት።
[35] ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።
[36] ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ።
[37] አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤
[38] ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።
[39] ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው።
[40] ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።
[41] እንግዲህ አይሁድ። ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና።
[42] አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ። ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ።
[43] ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ።
[44] የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።
[45] ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።
[46] አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል።
[47] እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።
[48] የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።
[49] አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤
[50] ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው።
[51] ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።
[52] እንግዲህ አይሁድ። ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ።
[53] ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።
[54] ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።
[55] ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።
[56] ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።
[57] ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።
[58] ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል
[59] በቅፍርናሆም ሲያስተምር ይህን በምኵራብ አለ።
[60] ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች በሰሙ ጊዜ። ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል? አሉ።
[61] ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ አላቸው። ይህ ያሰናክላችኋልን?
[62] እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?
[63] ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።
[64] ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ። ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና።
[65] ደግሞ። ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም አለ።
[66] ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም።
[67] ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ። እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ።
[68] ስምዖን ጴጥሮስ። ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤
[69] እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት።
[70] ኢየሱስም። እኔ እናንተን አሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ አይደለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው ብሎ መለሰላቸው።
[71] ስለ ስምዖንም ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ተናገረ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነ እርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አለውና።