[1] ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ።
[2] ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ደግሞ ስፍራውን ያውቅ ነበር።
[3] ስለዚህ ይሁዳ ጭፍሮችንና ከካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና በጋሻ ጦርም ወደዚያ መጣ።
[4] ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና። ማንን ትፈልጋላችሁ አላቸው።
[5] የናዝሬቱን ኢየሱስን ብለው መለሱለት። ኢየሱስ። እኔ ነኝ አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር።
[6] እንግዲህ። እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ።
[7] ደግሞም። ማንን ትፈልጋላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም። የናዝሬቱን ኢየሱስን አሉት።
[8] ኢየሱስ መልሶ። እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው አለ፤
[9] ይህም። ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን ስንኳ አላጠፋሁም ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
[10] ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ስለ ነበረው መዘዘው፥ የሊቀ ካህናቱንም ባርያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የባርያውም ስም ማልኮስ ነበረ።
[11] ኢየሱስም ጴጥሮስን። ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን? አለው።
[12] እንግዲህ የሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፥
[13] አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና።
[14] ቀያፋም። አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ይሞት ዘንድ ይሻላል ብሎ ለአይሁድ የመከራቸው ነበረ።
[15] ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤
[16] ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። እንግዲህ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው።
[17] በረኛ የነበረችይቱም ገረድ ጴጥሮስን። አንተ ደግሞ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን? አለችው። እርሱ። አይደለሁም አለ።
[18] ብርድ ነበረና ባሮችና ሎሌዎች የፍም እሳት አንድደው ቆሙ ይሞቁም ነበር፤ ጴጥሮስም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር።
[19] ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው።
[20] ኢየስስም መልሶ። እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፥ በስውርም ምንም አልተናገርሁም።
[21] ስለምን ትጠይቀኛለህ? ለእነርሱ የተናገርሁትን የሰሙትን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነዚህ እኔ የነገርሁትን ያውቃሉ አለው።
[22] ይህንም ሲል በዚያ ቆሞ የነበረው ከሎሌዎች አንዱ። ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን? ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው።
[23] ኢየሱስም መልሶ። ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ሰለ ምን ትመታኛለህ? አለው።
[24] ስለዚህ ሐና እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ሰደደው።
[25] ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። እንግዲህ። አንተ ደግሞ ከደቀ መዛሙርቱ አይደለህምን? አሉት። እርሱም። አይደለሁም ብሎ ካደ።
[26] ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ዘመድ የሆነ ከሊቀ ካህናቱ ባሮች አንዱ። በአትክልቱ ከእርሱ ጋር እኔ አይቼህ አልነበረምን? አለው።
[27] ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፥ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።
[28] ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ገዡ ግቢ ወሰዱት፤ ማለዳም ነበረ፤ እነርሱም የፋሲካ በግ ይበሉ ዘንድ እንጂ እንዳይረክሱ ወደ ገዡ ግቢ አልገቡም።
[29] ስለዚህ ጲላጦስ ወደ ውጭ ወደ እነርሱ ወጥቶ። ይህን ሰው ስለ ምን ትከሱታላችሁ አላቸው።
[30] እነርሱም መልሰው። ይህስ ክፉ አድራጊ ባይሆን ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር አሉት።
[31] ጲላጦስም። እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት አላቸው። አይሁድም። ለእኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም አሉት፤
[32] ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት ሊሞት እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
[33] ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? አለው።
[34] ኢየሱስም መልሶ። አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን? አለው።
[35] ጲላጦስ መልሶ። እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል? አለው።
[36] ኢየሱስም መልሶ። መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው።
[37] ጲላጦስም። እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ። እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው።
[38] ጲላጦስ። እውነት ምንድር ነው? አለው። ይህንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጥቶ። እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም።
[39] ነገር ግን በፋሲካ አንድ ልፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ እንግዲህ የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን? አላቸው።
[40] ሁሉም ደግመው። በርባንን እንጂ ይህን አይደለም እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።