[1] እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤
[2] በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው።
[3] ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል።
[4] የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤
[5] ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።
[6] ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደ ሆነ አላስተዋሉም።
[7] ኢየሱስም ደግሞ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ።
[8] ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም።
[9] በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል።
[10] ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።
[11] መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።
[12] እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል።
[13] ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል።
[14] -
[15] መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።
[16] ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።
[17] ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል።
[18] እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።
[19] እንግዲህ ከዚህ ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ሆነ።
[20] ከእነርሱም ብዙዎች። ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ? አሉ።
[21] ሌሎችም። ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዕውሮችን ዓይኖች ሊከፍት ይችላልን? አሉ።
[22] በኢየሩሳሌምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤
[23] ክረምትም ነበረ። ኢየሱስም በመቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር።
[24] አይሁድም እርሱን ከበው። እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን አሉት።
[25] ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤
[26] እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም።
[27] በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤
[28] እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም።
[29] የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።
[30] እኔና አብ አንድ ነን።
[31] አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ።
[32] ኢየሱስ። ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው።
[33] አይሁድም። ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት።
[34] ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔ። አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?
[35] መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥
[36] የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን። ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?
[37] እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤
[38] ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።
[39] እንግዲህ ደግመው ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም ወጣ።
[40] ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ እንደ ገና ሄደ በዚያም ኖረ።
[41] ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው። ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ።
[42] በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።