[1] በዚያን ጊዜም ጲላጦስ ኢየሱስን ይዞ ገረፈው።
[2] ወታደሮችም ከእሾህ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ አኖሩ ቀይ ልብስም አለበሱት፤
[3] እየቀረቡም። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ይሉት ነበር፤
[4] በጥፊም ይመቱት ነበር። ጲላጦስም ደግሞ ወደ ውጭ ወጥቶ። እነሆ፥ አንዲት በደል ስንኳ እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ አላቸው።
[5] ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ቀይ ልብስም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ።
[6] ጲላጦስም። እነሆ ሰውዬው አላቸው። የካህናት አለቆችና ሎሌዎች ባዩትም ጊዜ። ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትምና እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት አላቸው።
[7] አይሁድም መልሰው። እኛ ሕግ አለን፥ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባዋል፥ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና አሉት።
[8] ስለዚህ ጲላጦስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እግጅ ፈራ፤
[9] ተመልሶም ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን። አንተ ከወዴት ነህ? አለው። ኢየሱስ ግን አንድ እንኳ አልመለሰለትም።
[10] ስለዚህ ጲላጦስ። አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን? አለው።
[11] ኢየሱስም መልሶ። ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው አለው።
[12] ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን አይሁድ። ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው እያሉ ጮኹ።
[13] ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፥ በዕብራይስጥም ገበታ በተባለው ጸፍጸፍ በሚሉት ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ።
[14] ለፋሲካም የማዘጋጀት ቀን ነበረ፤ ስድስት ሰዓትም የሚያህል ነበረ፤ አይሁድንም። እነሆ ንጉሣችሁ አላቸው።
[15] እነርሱ ግን። አስወግደው፥ አስወግደው፥ ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። ንጉሣችሁን ልስቀለውን? አላቸው። የካህናት አለቆችም። ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም ብለው መለሱለት።
[16] ስለዚህ በዚያን ጊዜ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው።
[17] ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት፤ መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ።
[18] በዚያም ሰቀሉት፥ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሁለት፥ አንዱን በዚህ አንዱን በዚያ ኢየሱስንም በመካከላቸው ሰቀሉ።
[19] ጲላጦስም ደግሞ ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ ጽሕፈቱም። የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚል ነበረ።
[20] ኢየሱስም የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ነበረና ከአይሁድ ብዙዎች ይህን ጽሕፈት አነበቡት፤ በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ተጽፎ ነበር።
[21] ስለዚህ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን። እርሱ። የአይሁድ ንጉስ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ አሉት።
[22] ጲላጦስም። የጻፍሁትን ጽፌአለሁ ብሎ መለሰ።
[23] ጭፍሮችም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ሆኖ በአራት ከፋፈሉት፤ እጀጠባቡን ደግሞ ወሰዱ። እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም።
[24] ስለዚህ እርስ በርሳቸው። ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ። ይህም። ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
[25] ጭፍሮችም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር።
[26] ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት።
[27] ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።
[28] ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ። ተጠማሁ አለ።
[29] በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት።
[30] ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ። ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።
[31] አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ሆነ ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት።
[32] ጭፍሮችም መጥተው የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤
[33] ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤
[34] ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ።
[35] ያየውም መስክሮአል፤ ምስክሩም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል።
[36] ይህ የሆነ። ከእርሱ አጥንት አይሰበርም የሚል የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው።
[37] ደግሞም ሌላው መጽሐፍ። የወጉትን ያዩታል ይላል።
[38] ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ጲላጦስን ለመነ፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ።
[39] ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ።
[40] የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት።
[41] በተሰቀለበትም ስፍራ አትክልት ነበረ፥ በአትክልቱም ማንም ገና ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበረ።
[42] ስለዚህ መቃብሩ ቅርብ ነበረና ስለ አይሁድ ማዘጋጀት ቀን ኢየሱስን በዚያ አኖሩት።