Skip to content
Opens in a new window

[1] እንግዲህ። ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ያጠምቅማል ማለትን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ጌታ ባወቀ ጊዜ፥

[2] -

[3] ይሁዳን ትቶ ወደ ገሊላ ደግሞ ሄደ፤ ዳሩ ግን ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም።

[4] በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት።

[5] ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤

[6] በዚያም የያዕቆብ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ።

[7] ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም። ውኃ አጠጪኝ አላት፤

[8] ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና።

[9] ስለዚህ ሳምራዊቲቱ። አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና።

[10] ኢየሱስ መልሶ። የእግዚአብሔርን ስጦታና። ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት።

[11] ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?

[12] በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው።

[13] ኢየሱስም መልሶ። ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤

[14] እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት።

[15] ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ አለችው።

[16] ኢየሱስም። ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ አላት።

[17] ሴቲቱ መልሳ። ባል የለኝም አለችው። ኢየሱስ። ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፤

[18] አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት።

[19] ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ።

[20] አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም። ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው።

[21] ኢየሱስም እንዲህ አላት። አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል።

[22] እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን።

[23] ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤

[24] እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።

[25] ሴቲቱ። ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው።

[26] ኢየሱስ። የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት።

[27] በዚያም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን። ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም። ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም።

[28] ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች ለሰዎችም።

[29] ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን? አለች።

[30] ከከተማ ወጥተው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

[31] ይህም ሲሆን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ። መምህር ሆይ፥ ብላ ብለው ለመኑት።

[32] እርሱ ግን። እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው።

[33] ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ። የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን? ተባባሉ።

[34] ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው።

[35] እናንተ። ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ።

[36] የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፥ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል።

[37] አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና።

[38] እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ።

[39] ሴቲቱም። ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት።

[40] የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ሁለት ቀን ያህል ኖረ።

[41] ስለ ቃሉ ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤

[42] ሴቲቱንም። አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር።

[43] ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ።

[44] ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና።

[45] ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች ራሳቸው ደግሞ ለበዓል መጥተው ነበርና በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት።

[46] ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ።

[47] እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ ሰምቶ ልጁ ሊሞት ስላለው ወደ እርሱ ሄደ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው።

[48] ስለዚህም ኢየሱስ። ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም አለው።

[49] ሹሙም። ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለው።

[50] ኢየሱስም። ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ።

[51] እርሱም ሲወርድ ሳለ ባሮቹ ተገናኙትና። ብላቴናህ በሕይወት አለ ብለው ነገሩት።

[52] እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም። ትናንት በሰባት ሰዓት ንዳዱ ለቀቀው አሉት።

[53] አባቱም ኢየሱስ። ልጅህ በሕይወት አለ ባለው በዚያ ሰዓት እንደ ሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር አመነ።

[54] ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛ ምልክት ነው።

የዮሐንስ ወንጌል። — Chapters