Skip to content
Opens in a new window

[1] ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ።

[2] መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው።

[3] ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።

[4] ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው።

[5] ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።

[6] ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።

[7] ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ።

[8] ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።

[9] ኒቆዲሞስ መልሶ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው።

[10] ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?

[11] እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም።

[12] ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?

[13] ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።

[14] -

[15] ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።

[16] በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።

[17] ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።

[18] በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።

[19] ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው።

[20] ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤

[21] እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።

[22] ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር።

[23] ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥

[24] እየመጡም ይጠመቁ ነበር ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና።

[25] ስለዚህም በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ።

[26] ወደ ዮሐንስም መጥተው። መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ አሉት።

[27] ዮሐንስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ከሰማይ ካልተሰጠው ሰው እንዳች ሊቀበል አይችልም።

[28] እናንተ። እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን። ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ።

[29] ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ።

[30] እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል።

[31] ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው።

[32] ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፥ ምስክሩንም የሚቀበለው የለም።

[33] ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ።

[34] እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና።

[35] አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል።

[36] በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።

የዮሐንስ ወንጌል። — Chapters