Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:32

[1] እንግዲህ በኢየሱስ ክርስቶስ ላሉት በመንፈስ እንጂ በሥጋ ለማይመላለሱ ፍርድ የለባቸውም።

[2] በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠን ሕይወት የሚገኝበት የመንፈስ ሕግ እርሱ ከኀጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቶናልና።

[3] ስለ ሥጋ ደካማነት የኦሪት ሕግ ከሞት ማዳን በተሳነው ጊዜ እግዚአብሔር በኀጢኣተና ሥጋ ምሳሌ ልጁን ላከ፤ ያችንም ኀጢአት በሥጋው ቀጣት።

[4] እናን ያጸድቀን ዘንድ፥ የኦሪትንም ሕግ ሠርቶ እንደ ፈጸመ ሰው ያደርገን ዘንድ፤ ይህም በመንፈሳዊ ሕግ ጸንተው ለሚኖሩ ነው እንጂ በሥጋ ሕግ ለሚሠሩ አይደለም።

[5] እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ።

[6] የሥጋ ዐሳብ ሞትን ያመጣብናል፤ የመንፈስ ዐሳብ ግን ሰላምንና ሕይወትን ይሰጠናል።

[7] የሥጋ ዐሳብ ለእግዚአብሔር ጠላቱ ነውና፤ ለእግዚአብሔርም ሕግ ስለማይገዛ፥ መፈጸም አይቻለውም።

[8] ለሥጋዊ ፈቃዳቸው የሚሠሩ ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም።

[9] እናንተ ግን ለመንፈሳዊ ሕግ እንጂ ለሥጋችሁ ፈቃድ የምትሠሩ አይደላችሁም፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ አድሮ ይኖራልና፤ የክርስቶስ መንፈስ ያላደረበት ግን እርሱ የእርሱ ወገን አይደለም።

[10] ክርስቶስ ካደረባችሁ ግን ሰውነታችሁን ከኀጢአት ሥራ ለዩ፤ መንፈሳችሁንም ለጽድቅ ሥራ ሕያው አድርጉ።

[11] ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ ያስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረባችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ለይቶ ያስነሣው እርሱ አድሮባችሁ ባለ መንፈሱ ለሟች ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣታል።

[12] ወንድሞቻችን፥ አሁንም በሥጋችን ሳለን በሥጋ ፈቃድ እንኖር ዘንድ አይገባም።

[13] እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሥራ የሥጋችሁን ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራላችሁ።

[14] በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሠሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።

[15] ዳግመናም አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደ ገና ለፍርሀት የባርነት መንፈስን አልተቀበላችሁምና።

[16] እና የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆን ለልቡናችን ምስክሩ እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው።

[17] እና የእግዚአብሔር ልጆች ከሆን ወራሾቹ ነን፤ የእግዚአብሔር ወራሾች ከሆንም የክርስቶስ ወራሾቹ ነን፤ በመከራ ከመሰልነውም በክብር እንመስለዋለን።

[18] ነገር ግን የዚህ ዓለም መከራ ለእና ሊገለጥ ከአለው ክብር ጋር እንደማይተካከል ዐስቡ።

[19] የዓለም ተስፋው የእግዚአብሔርን ልጅ መምጣት ይጠባበቅ ነበርና።

[20] ዓለም ባለማወቅ ለከንቱ ነገር ተገዝቶአልና በተስፋ ስለ አስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም።

[21] ነገር ግን አስቶ በባርነት ከሚገዛው ከዚህ ወጥቶ የእግዚአብሔር ልጆች ወደ አገኙአት የነጻነት ክብር ይገባ ዘንድ ተስፋ አለው።

[22] እስካሁን ዓለም ሁሉ ያዘነና የተከዘ እንደ ሆነ እናውቃለን።

[23] ነገር ግን የሚተክዝ ዓለም ብቻ አይደለም፤ የመንፈስ ቅዱስን ፈለማ የተቀበልነው እናም ደግሞ እናዝናለን እንጂ፤ የነፍሳችንን ድኅነት እናገኝ ዘንድ የልጅነትን ክብር ተስፋ እናደርጋለንና፤ በእምነትም ድነናልና።

[24] የሚታየውን ተስፋ ማድረግ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ እንዴት ተስፋ ያደርጋል? እንዴትስ ይጠብቃል?

[25] የማይታየውን ተስፋ ብናደርግ ግን እርሱን ተስፋ አድርገን በእርሱ እንደ ጸናን መጠን ትዕግሥታችን ይታወቃል።

[26] መንፈስ ቅዱስም ከድካማችን ይረዳናል፤ እንግዲያስ ተስፋችንን ካላወቅን ጸሎታችን ምንድነው? ነገር ግን እርሱ ራሱ መንፈስ ቅዱስ ስለ መከራችንና ስለ ችግራችን ይፈርድልናል።

[27] እርሱም ልባችንን ይመረምራል፤ ልብ የሚያስበውንም እርሱ ያውቃል፤ ስለ ቅዱሳንም በእግዚአብሔር ዘንድ ይፈርዳል።

[28] እግዚአብሔር የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን።

[29] ልጁ በብዙዎች ወንድሞች መካከል በኵuር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸውንና የመረጣቸውን እነርሱን ልጁን ይመስሉ ዘንድ አዘጋጅቶአቸዋል።

[30] ያዘጋጃቸውን እነርሱን ጠራ፤ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፤ የአጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ።

[31] እንግዲህ ስለዚህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእና ጋር ከሆነ ማን ይችለናል?

[32] ለልጁ ስንኳ አልራራም፤ ስለ ሁላችን ቤዛ አድርጎ አሳልፎ ሰጠው እንጂ፥ እንግዲህ እርሱ ሁሉን እንዴት አይሰጠንም?

[33] እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማነው?

[34] የሚፈርድስ ማነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን ተለይቶ የተነሣው፥ በእግዚአብሔርም ቀኝ የተቀመጠው፥ ደግሞ ስለ እና የሚፈርደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

[35] ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? መራቆት ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን?

[36] መጽሐፍ እንዳለ ፥ “ስለ አንተ ዘወትር ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱ በጎችም ሆነናል።”

[37] ነገር ግን በወደደን በእርሱ ሁሉን ድል እንነሣለን።

[38] ነገር ግን ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ አለቆችም ቢሆኑ፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንደማይችል አምናለሁ።

[39] ኀይልም ቢሆን፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ሌላ ፍጥረትም ቢሆን ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል የለም።

ወደ ሮሜ ሰዎች። — Chapters