[1] ሰው ሁሉ በበላይ ላሉ ባለሥልጣኖች ይገዛ፤ ከእግዚአብሔር ከአልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።
[2] ለባለሥልጣን አልገዛም ያለ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንቢ ማለቱ ነው፤ መገዛትን እንቢ የሚሉም በራሳቸው ላይ ቅጣትን ያመጣሉ።
[3] ሹሞች ሥራው ክፉ ለሆነ ሰው እንጂ መልካም ለሚሠራ የሚአስፈሩ አይደሉም፤ ሹሞችን እንዳትፈራ ብትፈልግ መልካም አድርግ፤ እነርሱ ደግሞ ያመሰግኑሃል፤
[4] አንተ ሥራህን ታሳምር ዘንድ የእግዚአብሔር መልእክተኟች ናቸውና። ክፉ ብታደርግ ግን ፍራ፤ ሰይፍ የታጠቁም ለከንቱ አይደለም፤ ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና።
[5] ስለዚህ ቐጣን ስለ መፍራት ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው።
[6] ስለዚህም ግብር ታገቡላቸዋላችሁ፤ ለዚህ ሥራ የተሾሙ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና፤
[7] ለሁሉም እንደሚገባው አድርጉ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን ስጡ፤ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ስጡ፤ ዐሥራት ለሚገባው ዐሥራትን ስጡ፤ ሊፈሩት የሚገባውን ፍሩ፤ ክብር የሚገባውንም አክብሩ።
[8] እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ባልንጀራውን የወደደ ግን ሕግን ሁሉ ፈጸመ።
[9] በኦሪት እንዲህ ብሎአልና ፥ “አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፥ አትመኝ፤” ደግሞ ሌላ ትእዛዝ አለ፤ ነገር ግን የሁሉም ራስ “ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ ” የሚለው ነው።
[10] ባልንጀራዉን የሚወድ በባልንጀራዉ ላይ ክፉ ሥራ አይሠራም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።
[11] ከእንቅልፍ የምትነቁበት ጊዜ እንደ ደረሰ ዕወቁ፤ ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እና ደርሳለችና።
[12] ሌሊቱ አልፎአል፤ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማን ሥራ ከእና እናርቅ፤ የብርሃንንም ጋሻ ጦር እንልበስ።
[13] በቀን እንደሚሆን በጽድቅ ሥራ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር፥ በዝሙትና በመዳራትም አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን።
[14] ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ የሥጋችሁንም ምኟት አታስቡ።