Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:36

[1] እምነቱ ደካማ የሆነውን ሰው ታገሡት፤ በዐሳቡም አትፍረዱ።

[2] ሁሉን ይበላ ዘንድ እንደ ተፈቀደለት የሚያምን ሁሉን ይብላ፤ የሚጠራጠር ግን አትክልት ይብላ።

[3] የሚበላውም የማይበላውን አይናቀው፤ የማይበላውም የሚበላውን አይንቀፈው፤ ሁሉንም እግዚአብሔር አውቆአቸዋልና።

[4] እንግዲህ የሌላውን ሎሌ የምትነቅፍ አንተ ማነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለጌታው ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያነሣው ይችላልና ይቆማል።

[5] ከቀን ቀን የሚከለከል አለና፤ ዘወትርም የሚከለከል አለና፤ ነገር ግን ሁሉም ልቡ እንደ ወደደ ያድርግ።

[6] አንዳንድ ቀን የተከለከለም ለእግዚአብሔር ተከለከለ፤ ዘወትር የተከለከለም ለእግዚአብሔር ተከለከለ፤ የበላም ለእግዚአብሔር በላ፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግነዋል፤ ያልበላም ለእግዚአብሔር አልበላም፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግነዋል።

[7] ከመካከላችንም ለራሱ የሚኖር፥ ለራሱም የሚሞት የለም።

[8] በሕይወት ብንኖርም ለእግዚአብሔር እንኖራለን፤ ብንሞትም ለእግዚአብሔር እንሞታለን፤ እንግዲህ በሕይወት ብንኖርም ብንሞትም ለእግዚአብሔር ነን።

[9] ስለዚህ ሕያዋንንና ሙታንን ይገዛ ዘንድ ክርስቶስ ሞተ፥ ተነሣም።

[10] እንግዲህ በወንድምህ ላይ የምትፈርድ አንተ ምንድን ነህ? ወንድምህንስ የምትነቅፍ አንተ ምንድን ነህ? ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት እንቆማለንና።

[11] እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአልና ፥ “እኔ ሕያው ነኝ፤ ጕuልበትም ሁሉ ለእኔ ይሰግዳል፤ አንደበትም ሁሉ ለእኔ ይገዛል።”

[12] እነሆ፥ ሁላችን በእግዚአብሔር ዘንድ እንደምንመረመር ታወቀ።

[13] እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ እርስ በርሳችን አንነቃቀፍ፤ ይልቁንም ለወንድም እንቅፋትን ወይም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖር ይህን ዐስቡ።

[14] በራሱ ርኩስ የሆነ ነገር እንደሌለ በጌታችን በኢየሱስ ሆኜ ዐውቄአለሁ፤ ተረድቼአለሁም፤ ነገር ግን ማናቸውም ነገር ርኩስ እንደሚሆን ለሚያስብ ያ ለእርሱ ርኩስ ነው።

[15] በመብል ምክንያት ባልንጀራህን የምታሳዝን ከሆንህ ፍቅር የለህም፤ በውኑ ክርስቶስ ስለ እርሱ የሞተለት ያ ሰው በመብል ምክንያት ሊጐዳ ይገባልን?

[16] እንግዲህ ጌታችን የሰጠንን መልካሙን ነገር አታሰድቡ።

[17] የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም፤ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ነው እንጂ መብልና መጠጥ አይደለምና።

[18] እንዲህ አድርጎ ለክርስቶስ የሚገዛ ግን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና በሰውም ዘንድ የተመረጠ ነው።

[19] አሁንም ወንድማችን ይታነጽ ዘንድ ሰላምን እንከተላት።

[20] በመብል ምክንያት የእግዚአብሔርን ፍጥረት አናፍርስ፤ ለንጹሓን ሁሉ ንጹሕ ነው፤ ለሰውስ ክፉው ነገር በመጠራጠር መብላት ነው።

[21] ለወንድም ዕንቅፋት ከመሆን ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ይሻላል።

[22] እምነት ካለህ በእግዚአብሔር ፊት ባመንኸው እምነት ራስህን አጽና፤ ባገኘው አእምሮም ራሱን የሚዘልፍ ብፁዕ ነው።

[23] የሚጠራጠር ግን ቢበላ ይፈረድበታል፤ በማመን አልሆነምና፤ ያለ እምነትም የሚደረግ ሁሉ ኀጢአትና በደል ነው።

ወደ ሮሜ ሰዎች። — Chapters