[1] የሚገባስ እና ብርቱዎች ደካሞችን በድካማቸው እንድንረዳቸው ነው፤ ለራሳችንም አናድላ።
[2] ሁላችንም በእውነትና በመልካም ሥራ ይታነጽ ዘንድ ለባልንጀራችን እናድላ።
[3] ክርስቶስም ፥ “አንተን የነቀፉበት ነቀፋ በእኔ ላይ ደረሰ ” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ ለራሱ ያደላ አይደለም።
[4] የተጻፈው ሁሉ በመታገሣችንና መጻሕፍትን በመታመናችን ተስፋችንን እናገኝ ዘንድ እና ልንማርበት ተጻፈ።
[5] የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እግዚአብሔር እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ እርስ በርሳችን አንድ ዐሳብ መሆንን ይስጠን።
[6] ሁላችን አንድ ሆነን በአንድ አፍ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን እናመሰግነው ዘንድ።
[7] አሁንም ባልንጀሮቻችሁን ተቀበሉ፤ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር ተቀብሎአችኋልና።
[8] እንግዲህ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ለማድረግ የአባቶቻችንንም ተስፋ ያጸና ዘንድ ለግዝረት መልእክተና ሆነ እላለሁ።
[9] አሕዛብም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ ይቅር ብሎአቸዋልና፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና ፥ “አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ መካከል እገዛልሃለሁ፤ ስምህንም አመሰግናለሁ።”
[10] ዳግመናም መጽሐፍ እንዲህ ብሎአል ፥ “አሕዛብ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ።”
[11] ዳግመናም እንዲህ አለ ፥ “አሕዛብ ሁላችሁ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ ያመሰግኑታል።”
[12] ኢሳይያስም ደግሞ እንዲህ ብሎአል ፥ “የእሴይ ዘር ይነሣል፤ ከእርሱ የሚነሣውም ለአሕዛብ ንጉሥ ይሆናል፤ ሕዝቡም ተስፋ ያደርጉታል።”
[13] የተስፋ አምላክ እግዚአብሔርም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በተስፋ ያበዛችሁ ዘንድ በእምነት ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይፈጽምላችሁ።
[14] ወንድሞቼ ሆይ፥ እኔም በጎ ምግባርን ሁሉ እንደምትፈጽሙ እታመንባችኋለሁ፤ እናንተ ፍጹም ዕውቀትን የተመላችሁ ናችሁ፤ ባልንጀሮቻችሁንም ልታስተምሩአቸው ትችላላችሁ።
[15] ከእግዚአብሔር ስለ አገኘሁት ጸጋ ላሳስባችሁ በአንዳንድ ቦታ በድፍረት ጻፍሁላችሁ።
[16] በአሕዛብ መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን አገለግል ዘንድ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌልም እገዛ ዘንድ፥ በእኔ ትምህርት አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተወደደና የተመረጠ መሥዋዕት ይሆኑ ዘንድ።
[17] ለእኔም በእግዚአብሔር ዘንድ መመኪያዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
[18] አሕዛብም እንዲያምኑ ክርስቶስ በቃልም በሥራም ያደረገልኝን እናገር ዘንድ እደፍራለሁ።
[19] በኀይልና በተአምራት፥ በመንፈስ ቅዱስ ኀይልና ድንቅ ሥራን በመሥራትም፥ ከኢየሩሳሌም አውራጃዎች ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እንደ አስተማርሁ፥ የክርስቶስንም ወንጌል ፈጽሞ እንደ ሰበክሁ እናገር ዘንድ እደፍራለሁ።
[20] ወንጌልን ለማስተማር ተጋሁ፤ ነገር ግን በሌላ መሠረት ላይ እንዳላንጽ የክርስቶስ ስም ወደ ተጠራበት አልሄድሁም።
[21] “ወሬው ያልደረሳቸው ያውቁታል፤ ያልሰሙትም ያስተውሉታል” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ ነው።
[22] ዘወትር ወደ እናንተ ልመጣ እወድድ ነበር፤ ነገር ግን ተሳነኝ።
[23] አሁን ግን በዚህ ሀገር ሥራዬን ስለ ጨረስሁ፥ ከብዙ ጊዜም ጀምሮ ወደ እናንተ ልመጣ እተጋ ስለ ነበር፤
[24] ወደ አስባንያ ስሄድ እግረ መንገዴን ላያችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ቀደም ብዬ ከእናንተ ጋር ደስ ካለኝ በኋላም ከእናንተ ወደዚያ እሄዳለሁ።
[25] አሁን ግን ቅዱሳንን ለመርዳት ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ።
[26] መቄዶንያና አካይያ በኢየሩሳሌም ቅዱሳን መካከል ላሉ ድሆች አስተዋጽፅኦ ለማድረግ ተባብረዋልና።
[27] የሚገባቸውም ሰለሆነ በመንፈሳዊ ሥራ አሕዛብን ከተባበሩአቸው ለሰውነታቸው በሚያስፈልጋቸው ሊረዱአቸው ይገባል።
[28] እንግዲህ ይህን ፍሬ ጨርሼና አትሜ በእናንተ በኩል ወደ አስባንያ እሄዳለሁ።
[29] ነገር ግን በመጨረሻ ጊዜ በክርስቶስ ወንጌል በረከት ፍጹምነት እንደምትመጣ አምናለሁ።
[30] ወንድሞቼ፥ በጸሎታችሁ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ትተጉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ ፍቅር እማልዳችኋለሁ።
[31] ይኸውም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳንን በአገልግሎቴ ደስ አሰናቸው ዘንድ በይሁዳ ሀገር ካሉ ዐላውያን እንዲያድነኝ ነው።
[32] እግዚአብሔርም ቢፈቅድ በደስታ ወደ እናንተ መጥቼ ከእናንተ ጋር ዐርፍ ዘንድ ነው።
[33] የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።